ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እና አቶ አንዱዓለም አራጌ የኢዜማ መሪ ለመሆን ውድድር ጀመሩ
አቶ አንዱዓለም እና አርክቴክት ዮሐንስ የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ዛሬ ጀምረዋል
ፓርቲው፤ የአመራሮቹ ምርጫ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጿል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሰኔ መጨረሻ ላይ እንደሚያደርግ በሚጠበቀው 1ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የአመራሮች ምርጫ እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡
ፓርቲው በሚያደርገው ጉባዔ መሪ፣ ምክትል መሪ፣ ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር ፤ ዋና ጸሐፊና የፋይናስ ሃላፊዎችን እንደሚመርጥ ይጠበቃል፡፡ የፓርቲው አመራር ለመሆን ውድድር ከሚያደርጉት መካከል የወቅቱ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እና ምክትል መሪው አንዱዓለም አራጌ ይገኙበታል፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር ለመሆን ደግሞ የወቅቱ ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ፣ ጫኔ ከበደ (ዶ/ር)፣ ጫኔ ተመስገን፣ ጌታቸው ፓውሎስ እና ባንትይገኝ ታምራት (ዶ/ር) በዕጩነት ቀርበዋል፡፡
የኢዜማ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ትዕግስት ወርቅነህ የአመራሮቹ ይፋዊ የምረጡኝ ቅስቀሳ ከዛሬ ሰኔ አንድ እስከ ሰኔ 24 ቀን እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡ ለከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ምርጫ አመልካቾችን ከሚያዚያ 25 እስከ ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ.ም ሲቀበል የቆየው ፓርቲው፤ ለዕጩ ተወዳዳሪዎች ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ.ም ውጤታቸውን ማሳወቁን ገልጿል፡፡
የኢዜማ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ትዕግስት ወርቅነህ ይህ የአመራሮች አመራረጥ ሂደት፤ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው፤ ፓርቲው ለውስጠ ዴሞክራሲ ተገዥ መሆኑን እንደሚያሳይም ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
የአመራረጥ ሂደቱ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተለመደ ባይሆንም ብዙ ሊያስተምር የሚገባ እንደሆነ ያነሱት ኃላፊዋ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስት መሪም ሆነ የድርጅት መሪ ለመሆን ሃሳብን ማቅረብና ውድድር ማድረግ መለመድ እንዳለበትም ነው ሃላፊዋ የጠቀሱት፡፡
የአመራሮች ምርጫ በኢትዮጵያ የፓርቲዎች የውስጥ አመራር አመራረጥ ታሪክ ላይ አስተማሪ ሆኖ እንዲያልፍ አባሎቹና ደጋፊዎቹ ሕግ እና ስርዓት እንዲከበር አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል፡፡
የወቅቱ የፓርቲው ምክትል መሪ አንዱዓለም አራጌ እንዲሁም አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ዛሬ ይፋዊ የምርጡኝ ቅስቀሳ ጀምረዋል፡፡ በውድድሩ አርክቴክት ዮሐንስ ለመሪነት እየተወዳደሩ ላሉት ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) ምክትል፤ አቶ ሀብታሙ ኪታባ ደግሞ ለመሪነት እየተወዳደሩ ላሉት አቶ አንዱዓለም አራጌ ምክትል ለመሆን ውድድር ጀምረዋል፡፡
አርክቴክት ዮሐንስ ፤ ከምርጫው ባሻገር “የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያችንን መገንባት፤ ሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫን በተግባር ማሳየትና በሀገር ዐቀፍ ደረጃ የዴሞክራሲ ባህል ሥር እንዲሰድ ያለንን ጽኑ ፍላጎት ማስመስከር አለብን” በማለት ይፋዊ ቅስቀሳ ጀምረዋል፡፡
አቶ አንዱዓለምም ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት የሚደረገው የምረጡኝ ቅስቀሳ ለኢዜማ ብሎም ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተስፋ እንደሚደርጉ ገልጸዋል። በዚህም መሰረት እርሳቸው ለመሪነት፤ ሀብታሙ ኪታባ ደግሞ ለምክትል መሪነት በሚያደርጉት ቅስቀሳ መሪ ቃላቸው “ለኢዜማ ዓላማ፤ በኢዜማዊ ቀለም” መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
ኢዜማ ከዚህ ቀደም የመስራች እንዲሁም አስቸኳይ ጉባዔዎችን ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን በያዝነው ወር መጨረሻ ደግሞ የመጀመሪያ መደበኛ ጉባዔውን እንደሚደርግ ቀነ ቀጠሮ ይዟል፡፡