አዲስ አበባን ለአምስት አመት የሚያስተዳድር አዲስ መንግስት ዛሬ ተመስርቷል
በአዲስ አበባ ከተማ የአዲስ መንግስት ምስረታ ተካሂዷል፤ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም በድጋሚ የከተማዋ ከንቲባ በመሆን ተመርጠዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሥራ አስፈጻሚ አባልን በካቢኔያቸው ውስጥ አካተቱ፡፡
ከንቲባዋ የአብን ምክትል ሊቀመንበር የሱፍ ኢብራሒምን የመንግሥት ንብረት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የኢዜማ ስራ አስፈጻሚ አባል ግርማ ሠይፉን የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር በማድረግ ካቢኔያቸው ውስጥ አካተዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ቀንዓ ያደታ (ዶ/ር) ከፌዴራል ሃላፊነታቸው ወደ አዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሲመጡ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር የነበሩት ሂሩት ካሳውም (ዶ/ር) በተመሳሳይ ከፌዴራል ኃላፊነት ተነስተ የአዲስ አበባ የባህል፤ኪነጥበብ ና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ በመሆን የመዲናዋ ካቢኔ አባል ሆነዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አቶ ጃንጥራር አባይ ምክትል ከንቲባና የስራ፤ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የነበሩት ዮናስ ዘውዴ የአዲስ አበባ ከተማ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ ሆነው ተሸመዋል፡፡
በሰኔ 14፣2013ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ፤ አብላጫ ድምጽ ያገኘው ብልጽግና ፖርቲ በመጭው መስከረም 24 ኢትዮጵያ ለአምስት አመታት የሚመራ ምንግስት ይመሰርታል፡፡