ኢዜማ የመንግስትን እስረኞችን የመፍታት ውሳኔ ተቃወመ
መንግስት ከእንዲህ ዐይነት እርምጃዎች ሊቆጠብ ይገባል ያለም ሲሆን ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ በጥቂት ኃይሎች እንዳይዘወር የበኩላችንን እንወጣ ሲል ጥሪ አቅርቧል
“ግብታዊ” ባለው ክስ አቋርጦ እስረኞችን የመልቀቅ እርምጃ መንግስት ይቅርታ መጠየቅ አለበትም ብሏል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአጥፊነት ተጠርጥረው እና በጦር ግንባር ተይዘው በሕግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎችን ክስ በማቋረጥ ከእስር መለቀቃቸውን ተቃወመ፡፡
ተበዳይ ፍትህ ሳያገኝ እንዲሁም ሳይካስ በዳይን ነፃ ማውጣት በፍትህ ስርዓቱ መቀለድ፣ የሕዝባችንን ጉዳትም ማቃለል ነው ሲል መግለጫ ያወጣው ኢዜማ በጥድፊያ የሚደረጉ እንዲህ ዐይነት ውሳኔዎች ፍትህን በመጨፍለቅ በተቋማቱ ላይ ያለንን እምነት በሂደት የሚሸረሽሩ ናቸው ብሏል፡፡
ካለ ህዝባዊ ምክክር የተደረገ ነው ያለው ይህ “ግብታዊ” እርምጃ አመፀኝነትን የሚያበረታ እና መከፋፈልን የሚያጠነክር እጅጉን አሳሳቢ ተግባር እንደሆነም ገልጿል፡፡
በዚህ ወቅት የጦርነቱን ገፈት ቀማሾች ማቀራረብ እና ብሔራዊ እርቅን መፈፀም እጅጉን ወሳኝና የሚጠበቅ ቢሆንም በየአካባቢው ያለው ሕዝብ “ትኩስ ሬሳን ተሸክሞ ባለበት፣ የሚፈሰው ደሙ ባልረጋበት፣ የተደፈሩ እናቶች፣ እህቶች እና ልጆች ከስቃያቸው ባላገገሙበትና የተፈናቀሉ ወገኖች ወደቀያቸው ባልተመለሱበት” ሁኔታ በአጥፊነት ተጠርጥረው እና በጦር ግንባር ተይዘው በሕግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎችን ክስ ማቋረጥ እና ምህረት ብሎ በዳይን መካስ “እጅግ የሚያስቆጭ እና የሚያንገበግብ እውነት” እንደሆነ ገልጿል፡፡
መንግሥት ከዚህ ድርጊቱ መቆጠብ ብቻም ሳይሆን በይፋ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታልም ነው ኢዜማ ያለው፡፡
የፍትህ ስርዓቱ “በደመነፍስ ከመስራት ተሻግሮ” ለዜጎች ፍትህን የሚያሰፍን ሆኖ ሊደራጅ እንደሚገባዋውም አሳስቧል፡፡
መንግሥት እጅግ የማይገመቱ እና ሀገሪቷን እና የሕዝቧን የትኩረት አቅጣጫ በእጅጉ የሚያስቀይሩ ኃላፊነት የጎደላቸው እና ከማን አለብኝነት የሚነሱ ተግባራትን ከመፈፀም በፍጥነት ይቆጠብ ሲልም አሳስቧል፡፡
ጦርነቱ ባልተቋጨበት እና የሕዝቡ መስዋዕትነት ባልቆመበት ሁኔታ ጦርነቱ እንዳለቀ ተደርጎ መቅረቡንም ተቃውሟል፡፡
አካሄዱ ዜጎችን በማዘናጋት ከቀድሞው የከፋ መስዋዕትነት የሚያስከፍል የስህተት አካሄድ በመሆኑ ታርሞ አሁንም ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በንቃት መጠበቅ ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብሏል፡፡
ኢዜማ ታህሳስ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ ድርድሮች እና ሀገራዊ ምክክር ተደበላልቀው እንዳይሄዱ ማሳሰቡን በማስታወስም መንግሥት ሁለቱን ጉዳዮች አጣብቆ ለማስኬድ ያለው ፍላጎት አሁን አሁን በግልፅ እየታየ መጥቷል ብሏል፤ ትርፉ ኪሳራ እንደሆነ በማሳሰብ፡፡
“በአሁን ሰዓት ከገባንበት ቅርቃር መውጫችን ሃገራዊ ምክክር ነው” ያለም ሲሆን መላውን ሕዝብ ያሳተፈ እውነተኛ ምክክር እንዲደረግ ቆራጥነት ይጎድላል ብሏል በመግለጫው፡፡
መንግሥት ሂደቱን ለመጥቀም ነው እያለ የሚፈፅማቸው አንዳንድ ተግባራት ሂደቱ ላይ ትልቅ ጠባሳ ሊጥሉ እና ወደ ኋላ ሊጎትቱት የሚችሉ ተገማች ያልሆኑ ውሳኔዎች እንደሆኑም ገልጿል፡፡
እንዲህ ዓይነት አካሄዶች ሂደቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመንግሥት ተፅዕኖ ስር እንዲገባ ስለሚያደርጉ በፍጥነት ይታረሙ ሲልም መንግሥትን አሳስቧል፡፡
ከገጠመው ችግር ለመውጣት ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ይጠበቅብናል ያለም ሲሆን የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት በጥቂት ኃይሎች እንዳይዘወር የበኩላችንን እንወጣ ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡
መንግስት ሀገራዊ ምክክሩን አካታች ለማድረግ በሚል ከሰሞኑ የተወሰኑ እስረኞችን መፍታቱ የሚታወስ ነው፡፡
እናት ፓርቲ ህጋዊ አይደለም ያለውን የመንግስትን ውሳኔ ተቃውሞ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡