ኢዜማ ወጣቶች የሀገር ጠባቂ መሆናቸውን ተረድተው “ሀገራቸውን ለማፍረስ ከተነሱ አማፂ ኃይሎች መከላከል” ይኖርባቸዋል አለ
ኢዜማ መንግስት፤ ከመንግስት መዋቅር ውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ጭምር የሚያሳትፍ "ብሔራዊ የሀገር ሉዓላዊነት እና የሕዝብ ደህንነት ማሰከበር ዘመቻ ግብረ ኃይል" የተሰኘ ግብረ ኃይል በአስቸኳይ እንዲያቋቁም እና ወደ ሥራ እንዲገባ ኢዜማ ጠይቋል።
ፓርቲው ዛሬ በሰጠው መግለጫ በሀገር ላይ የተጋረጠ አደጋን በብቃት ለመመከት እና ለማስቀረት ሁሉንም በአንድነት አሰባስቦ ማሰለፍ የሚችለው የፌደራል መንግሥት በመሆኑ መንግሥት ይህን ግዴታውን መወጣት አለበት ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነትና ያስከተለውን ችግር በውጤታማነት ማለፍ እንዲቻል የወታደራዊ፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ የፕሮፖጋንዳ፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረዱበትንና በኢኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስትራቴጂ የሚነድፍና ውሳኔ የሚያስተላልፍ ግብረ ኃይል ያስፈልጋል ብሏል ኢዜማ በመግለጫው፡፡
ኢዜማ “ወጣቶች የሀገር ባለቤት እና ጠባቂ መሆናቸውን ተረድተው ሀገራቸውን በማንአለብኝነት ለማፍረስ ከተነሱ አማፂ ኃይሎች መከላከል” ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡
በጥቅምት ወር 2013 የህወሓት ሃይሎች በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ባወጀው የህግ ማስከበር ዘመቻ ተጀመረው ግጭት አሁን ላይ 11 ወራት ሊሆነው ነው፡፡
የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፣ ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱን ተከትሎ የህወሓት ሃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምረው በርከታ ቦታዎች መቆጣጠር ችለዋል፡፡ትግራይን የተቆጣጠሩት የትግራይ ሃይሎች፤ ወደ አጎራባችና አማራና አፋር ክልል ጥቃት ከፍተው ቦታዎች ተቆጣጥረዋል፡፡
የህወሓት ኃይሎች ወደ አጎራባቸው ክልሎች ጥቃት መክታቸውን ተከትሎ የአማራ ክልል መንግስትና የፌደራል መንግስት የህወሓት ሃይሎችን ለመዋጋት የዘመቻ ጥሪ አቅርበዋል፤ጦርነትም እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የህወሓት ሃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመግባት ጥቃት በማድረሳቸው ከ300ሺ በላይ ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸውንና የተናጠል ተኩስ አቁሞ የተፈለገውን ለውጥ አላመጣም ያለው የፌደራል መንግስት መከላከያ ሰራዊትና የክልል ልዩ ሃይሎች ጠንካራ እርምጃ እንዲወስዱ አቅጣጫ ማስቀመጡን ባለፈው ሳምንት መግለጹ ይታወሳል፡፡