ከመንግስት ጋር መስራት የማንኛውም “ጤነኛ ፓርቲ ባህሪ መሆን አለበት”-የኢዜማ ሊቀመንር የሽዋስ አሰፋ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት 2010 ዓ.ም በኋላ በኢትዮጵያ መጣ የተባው ፖለቲካዊ “ለውጥ” በተጠበቀው መልኩ እየቀጠለ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (አዜማ) ገለጸ።
የኢዜማ ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ለውጡ” በብዙ ኃይሎች ጥረት ዕውን ቢሆንም በተጠበቀው ልክ እየሄደ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ሊቀመንበሩ ለውጡ በሚፈለገው መጠን ያልተሳካው በብዙ መሰናክሎች እንደሆነ ገልጸው መሰናክሉ ግን የአንድ ወገን ብቻ አይደለም ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ በተጠበቀው መጠን አለመሳካቱ አስደንጋጭ እንደሆነም ፖለቲከኛው አንስተዋል፡፡
ኢዜማ ከመንግስት ጋር መስራቱ በሚያራምደው የፖለቲካ ስራ ላይ ጫና ይፈጥርበታል ወይ በሚል ለቀረበው ጥያቄ ፤ ከመንግስት ጋር መስራት የማንኛውም “ጤነኛ ፓርቲ ባህሪ መሆን አለበት፤ ነውም ብለን እናምናለን” ሲሉ ሊቀመንበሩ መልሰዋል።
ፓርቲው የፓርቲ እና የመንግስት መዋቅር የለየው ገና ሲመሰረት እንደሆነ ያነሱት አቶ የሺዋስ በመንግስት ሹመት የተሰጣቸው ግለሰቦች የገቡት መንግስት መዋቅር ውስጥ እንጅ ገዥው ፓርቲ ባለመሆኑ ስጋት እንደማያመጣ ገልጸዋል፡፡ ከኢዜማ ወደ መንግስት የኃላፊነት ቦታዎች የገቡ ሰዎች በመንግስት ወገን ሊሆኑ እንደሚችሉ ቀደም ብለው የተዘጋጁ አንደሆነም አቶ የሺዋስ ጠቅሰዋል፡፡
ኢዜማ ከመንግስት ጋር የሚወዳደርበትንና የሚተባበርበትን መንገድ “በደንብ” እየለየ እንደሆነ የሚናገሩት ሊቀመንበሩ፤ፓርቲያቸው የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት እንዲቀጥል እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡ አቶ የሺዋስ አሁን ያለው ስርዓት ጸጥታ የማስከበር ስራውን በሚፈለገው መጠን አለመስራቱን ገልጸው ይህ እንዲሻሻልም ኢዜማ ትግል እንደሚደርግ አስታውቀዋል፡፡
የመንግስት ትንሹ ስራ ወይም አስፈላጊነት መጀመሪያ ጸጥታ ማስከበር ቢሆንም ብልጽግና ፓርቲ ግን በምርጫ 2013 ክርክር ላይ የጸጥታ ችግርን የሀገሪቱ መሰረታዊ ችግር ብሎ አለማካተቱን አንስተዋል፡፡ ኢዜማ እና ብልጽግና በዋናነት ልዩነታቸው ብልጽግና ጸጥታ ችግርን አቅልሎ በማየቱ እንደሆነም አቶ የሺዋስ አንስተዋል፡፡ “ሀገርን ከውጭ ወራሪም ከውስጥ ቦርቧሪም መጠበቅ የመንግስት ትንሹ ስራ ነው” ያሉት ሊቀመንበሩ ልማትና ዴሞክራሲ አስተማማኝ ጸጥታ በሌለበት ሊታሰብ የማይችል ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት “ሰው ዘቅዝቅው የገደሉ ሰዎች፤ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተሞከረው የግድያ ሙከራ፣ ቢሾፍቱ ላይ የተገደለው የኢዜማ ተወካይና ሌሎችም…” ተጣርተው ተገቢ ፍርድ አለመሰጠቱ ወንጀሎች እንዲበራከቱና ወንጀለኞች እንዲበረታቱ እንደሚደርግም ሊቀመንበሩ ጠቅሰዋል፡፡
ኢዜማ ተመርጦ ቢሆን ኖሮ ለጸጥታ ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ያስተካክል እንደነበርም ነው ሊቀመንበሩ የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (አዜማ) በምርጫ 2013 ከተሳተፉ ፓርቲዎች አንዱ ሲሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር ካገኙ ፓርቲዎች አንዱ ነው፡፡
መንግስትን የሚመራው ብለጽግና ፓርቲ በቅርቡ ያካሄደውን ጉባኤ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ የመላው ኢትዮጵያውያንን ማህበራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ እንደሚንቀሳቀስ መግለጹ ይታወሳል፡፡
ፓርቲው በጦርነት እና በግጭት ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚያደርግና እና ሰላምን የሚያውኩ የሽብር እና የጽንፈኝነት ዝንባሌዎች በእንጭጩ ይቀጫል ብሏል።