
የዶናልድ ትራምፕ መመረጥ ለቢትኮይን ዋጋ መጨመር ትልቅ ምክንያት ሆኗል
የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ከ100 ሺህ ዶላር ተሻገረ።
ከአንድ ዓመት በፊት የአንድ ቢትኮይን ዋጋ 44 ሺህ ዶላር የነበረ ሲሆን አሁን ላይ 100 ሺህ ዶላር አልፏል።
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ ከአንድ ወር በፊት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተካሄደ ሲሆን የሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ በሰፊ ልዩነት አሸንፈዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ የቢትኮይን ደጋፊ መሆናቸውን በይፋ ከተናገሩ በኋላ የቢትኮይን ዋጋ በፍጥነት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።
የምርጫው ዋዜማ ዕለት አንድ ቢትኮይን በ 68 ሺህ ዶላር ይሸጥ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ አንድ ቢትኮይን በ30 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ በ103 ሺህ ዶላር እየተሸጠ ይገኛል።
የአሁኑ የቢትኮይን ዋጋ በታሪክ ከፍተኛው ተብሎ እንደተመዘገበ ብሉምበርግ ዘግቧል።
ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ የዓለም ቢትኮይን ግብይት ማዕከል የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እንደ ቢትኮይን አይነት ግብይቶችን ለማበረታታት የግብር ቅናሽ እና ሌሎች ድጋፎችን እንደሚያደርጉ ትራምፕ ተናግረዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ከሶስት ዓመት በፊት ስለ ቢትኮይን ለቀረበላቸው ጥያቄ "ቢትኮይን ቁማር ነው እንዳትታለሉ ይቅርባችሁ ሲሉ ተናግረው ነበር።
ጥር አጋማሽ ላይ ስራ እንደሚጀመር የሚጠበቀው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር የካቢኔ አባላት መረጣው እንደቀጠለ ሲሆን ኢለን መስክን ጨምሮ እንደሚሾሙ የሚጠበቁት ሀላፊዎች የክሪፕቶ ከረንሲ ግብይቶችን የሚደግፉ ናቸው፡፡