120 ሺህ የሚጠጋ ቢትኮይን የዘረፈው አሜሪካዊ በእስራት ተቀጣ
በአለማችን ትልቁን የምናባዊ መገበያያ (ክሪፕቶከረንሲ) ዝርፊያ የተሳተፈው ኢልያ ሊችተንስታይን በአምስት አመት እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ሲውል የዘረፈው ቢትኮይን ዋጋ 4.5 ቢሊየን ዶላር ያወጣ ነበር ተብሏል
በአለማችን ግዙፍ ከተባለው የምናባዊ መገበያያ (ክሪፕቶከረንሲ) ዝርፊያ የተሳተፈው አሜሪካዊ በአምስት አመት እስራት ተቀጣ።
ኢልያ ሊችተንስታይን የተባለው ግለሰብ በ2016 ቢትፊኔክስ በተሰኘው የክሪፕቶከረንሲ ዝርፊያ የተገኘውን ገንዘብ በማዘዋወር ተከሶ ባለፈው አመት ጥፋተኛ መባሉ ይታወሳል።
በወቅቱ የተሰረቀውን 120 ሺህ የሚጠጋ ቢትኮይን ከባለቤቱ ሄዘር ሞርጋን ጋር በመሆን ማዘዋወሩ መገለጹም አይዘነጋም።
የቢትፊኔክስ ክሪፕቶከረንሲ ተጠልፎ ዝርፊያው ሲፈጸም የተዘረፈው ቢትኮይን የገበያ ዋጋ 70 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ነበር።
በየካቲት ወር 2022 ሊችተንስታይን እና ባለቤቱ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ግን የቢትኮይኑ ዋጋ ወደ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ማደጉን ቢቢሲ ዘግቧል። በአሁኑ የቢትኮይን ዋጋ ደግሞ ከዚህ በብዙ እጥፍ የሚልቅ ዋጋ አለው።
ዘራፊዎቹ ሲያዙ 3.6 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያለው ቢትኮይን መገኘቱና ይህም በአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ታሪክ ከፍተኛው መጠን ያለው ገንዘብ ነው መባሉ የሚታወስ ነው።
ከሁለት አመት በፊት በቁጥጥር ስር ውሎ በእስር የሚገኘው ኢልያ ሊችተንስታይን በፈጸመው ድርጊት መጸጸቱን ተናግሯል።
የተላለፈበትን እስራት ካጠናቀቀ በኋላም የኮምፒውተር ክህሎቱን የሳይበር ወንጀሎችን ለመከላከል እንደሚያውለው ለችሎት አስረድቷል።
የሂፕ ሆፕ ሙዚቃ አቀንቃኟ ባለቤቱ ሄዘር ሞርጋንም ባለፈው አመት በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ጥፋተኛ የተባለች ሲሆን ከሶስት ቀናት በኋላ የቅጣት ውሳኔ ይተላለፍባታል።
የፍርድቤት ሰነዶች እንደሚያመላክቱት ሊችተንስታይን በ2016 የተፈጸመውን የቢትፊኒክስ ዝርፊያ ለማከናወን እጅግ የዘመኑ የጠለፋ መሳሪያዎች እና ቴክኒኮች ተጠቅሟል።
የተጠለፈውን ቢትኮይን ለማዘዋወርም ከባለቤቱ ሞርጋን ጋር በመሆን በርካታ አካውንቶችን መክፈቱንና የወርቅ ሳንቲሞችን መግዛቱንም ነው ሰነዶቹ የጠቆሙት።
በሩሲያ ተወልዶ በአሜሪካ ያደገው ሊችተንስታይን ከቤተሰቦቹ ጋር ለጉብኝት ወደ ሩሲያ ባቀናበት ወቅት ገንዘቡን የሚያዘዋውርበት መንገድ እያፈላለገ እንደነበርም ተገልጿል።