የሀገራት ቢትኮይን ግብይት እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል ተገልጿል
የአንድ ቢትኮይን ዋጋ አንድ ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል ተባለ፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት የአንድ ቢትኮይን ዋጋ 44 ሺህ ዶላር የነበረ ሲሆን ከሰሞኑ 103 ሺህ ዶላር ደርሷል መባሉ ይታወሳል።
ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ተደርገው መመረጣቸውን ተከትሎ የምናባዊ ገንዘብ ወይም ክሪፕቶከረንሲ ዋጋ እየጨመረ ይገኛል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ የቢትኮይን ደጋፊ መሆናቸውን በይፋ ከተናገሩ በኋላ የቢትኮይን ዋጋ በፍጥነት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።
ከአንድ ወር በፊት በተካሄደው የአሜሪካ ምርጫ ዋዜማ ዕለት አንድ ቢትኮይን በ 68 ሺህ ዶላር ይሸጥ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ አንድ ቢትኮይን በ98 ሺህ ዶላር እየተሸጠ ይገኛል።
ባሳለፍነው ሳምንት የአንድ ቢትኮይን ዋጋ 103 ሺህ ዶላር ደርሶ የነበረ ሲሆን ይህም በታሪክ ከፍተኛው ተብሎ ተመዝግቧል።
በዱባይ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የክሪፕቶከረንሲ ጉባኤ ላይ የተገኙት የዶናልድ ትራምፕ ልጅ የሆኑት ኤሪክ ትራምፕ የአንድ ቢትኮይን ዋጋ አንድ ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ብሉምበርግ በበኩሉ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የአንድ ቢትኮይን ዋጋ አንድ ሚሊዮን እንደሚደርስ ዘግቧል፡፡
የቢትኮይን ግብይትን የሚፈቅዱ ሀገራት መጨመር፣የክሪፕቶከረንሲ ግብይት መሰረተ ልማት መስፋፋት እና አዳዲስ ፖሊሲዎች መቀረጽ ለምናባዊ ግብይቶች መጨመር በጎ ሚና ይጫወታሉም ተብሏል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ የዓለም ቢትኮይን ግብይት ማዕከል የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት መናገራቸው ይታወሳል፡፡