ጥቁር ሴቶች በጡት ካንሰር የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ጥናት አመላከተ
ጥቁር ሴቶች በ42 ዓመታቸው በቋሚነት የጡት ካንሰር ምርመራ እንዲጀምሩ ነው ጥናቱ ያሳሰበው
በአሜሪካ ብቻ ባለፉት 8 ዓመታት ውስጥ ከ415 ሺህ በላይ ሴቶች በጡት ካንሰር ህይወታቸውን አጥተዋል ተብሏል
ጥቁር ሴቶች በጡት ካንሰር የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።
የአሜሪካው በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ወይም ሲዲሲ ባወጣው ጥናት ጥቁር ሴቶች ከነጮች ጋር ሲነጻጸሩ በጡት ካንሰር የመሞት እድላቸው የበለጠ ጨምሯል።
በዚህ ጥናት መሰረት ከ100 ሺህ ጥቁር ሴቶች ውስጥ 27 ሴቶች በጡት ካንሰር ይሞታሉ።
በአንጻሩ ከ100 ሺህ ነጭ ሴቶች ውስጥ በጡት ካንሰር የሚሞቱት 15ቱ ብቻ ናቸው ተብሏል።
ሴቶች በማንኛውም እድሜያቸው የጡት ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ ቢመክርም ከ42 ዓመታቸው ጀምሮ ግን በቋሚነት እንዲመረመሩ ጥናቱ ይጠቁማል።
ይሁንና ጥናቱ ለምን ጥቁር ሴቶች ከነጮች ጋር ሲነጻጸር የበለጠ በጡት ካንሰር ሊሞቱ እንደቻሉ አላብራራም።
የጥናቱ ደራሲ እና በጀርመን ካንሰር ጥናት ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ማህዲ ፋላን ለሲኤንኤን እንዳሉት በጡት ካንሰር የሚያዙ ነጭ ሴቶች ቁጥር ከጥቁር ሴቶች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ቢሆንም በሞት መጠን ግን የጥቁር ሴቶች ከፍተኛ ነው።
ዶክተር ማህዲ አክለውም ፖሊሲ አውጪዎች በጡት ካንሰር የሚሞቱ ጥቁር ሴቶች ለምን እንደጨመረ ሊመረምሩ ይገባል ብለዋል።
ጥቁር ሴቶች በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋማት አለመምጣት፣ በኢኮኖሚ ድቀት እና በሌሎችም ምክንያቶች በበሽታው የመያዝ እና የመሞት ምጣኔያቸው ሊጨምር እንደሚችልም ተመራማሪው ጠቅሰዋል።
በቻይና፣ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን እና ኖርዌይ ትኩረቱን ያደረገው ይህ ጥናት ከፈረንጆቹ 2011 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት ውስጥ በጡት ካንሰር የሞቱ ሴቶችን መረጃ በግብዓትነት መውሰዱ ተገልጿል።