የሳንባ ካንሰር የማያጨሱ ሰዎችን ጭምር እንደሚያጠቃ ያውቃሉ?
የሳንባ ካንሰር ምልክቱን ቀድሞ የማያሳይና በየአመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት የሚዳርግ በሽታ ነው
ለሶስት ሳምንት የዘለቀ ሳል፣ የድምጽ መሻከር እና ለመዋጥ መቸገር ከሳንባ ካንሰር ምልክቶች መከካል ይጠቀሳሉ
ትንባሆ ማጨስ በየአመቱ ከ8 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ህይወት እንደሚቀጠፍ የአለም ጤና ድርጅት ይገልጻል።
በኢትዮጵያም በትንባሆ ጭስ ምክንያት በዓመት 17 ሺህ ሰዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ ነው የሚነገረው።
በየቀኑ በአማካይ 350 ሰዎች በሳንባ ካንሰር ምክንያት ህይወታቸው የሚያጡባት አሜሪካም፥ የሳንባ ካንሰር ከሁሉም የካንሰር በሽታዎች በበለጠ አሳሳቢነቱ ጨምሯል ትላለች።
በሳንባ ካንሰር ከሚጠቁት ውስጥ ከ70 ከመቶ በላዩ የሚያጨሱ ሰዎች መሆናቸውን የብሪታንያው ብሄራዊ የጤና አገልግሎት (ኤን ኤች ኤስ) አስታውቋል።
ይሁን እንጂ የማያጨሱ ሰዎችም በሳንባ ካንሰር ሊጠቁ እንደሚችሉ በጥናት ተደርሶበታል ነው ያለው።
በየአመቱ በትንባሆ ጭስ ምክንያት ህይወታቸው ከሚያልፍ ሰዎች ውስጥ ከ1 ሚሊየን በላዩ የማያጨሱ መሆናቸውን የአለም ጤና ድርጅት ባለፈው አመት ባወጣው ጥናት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በተለይ እድሜያቸው ከ75 አመት በላይ በሆኑ አዛውንቶች ላይ መስተዋል ጀምሯል፤ ከአስር በሳንባ ካንሰር ከተያዙ ሰዎች ውስጥ አራቱ እድሜያቸው ከ75 አመት በላይ ነው ይላል ኤን ኤች ኤስ።
የበሽታው ምልክቶች ካንሰሩ በሳንባ እና ሌሎች የሰውነታችን ክፍሎች በደንብ እስኪሰራጭ ድረስ የሚታዩ አለመሆናቸውም ድምጽ አልባ ገዳይ በሽታ ያደርገዋል ነው የተባለው።
በሳንባ ካንሰር ከተጠቁ አምስት ሰዎች ሁለቱ በካንሰር መያዙን ካወቁ በኋላ በህይወት የሚቆዩት ለአንድ አመት ብቻ ነው ይላል ዴይሊ ሜል ላይ የሰፈረው የጥናት ውጤት።
የሳንባ ካንሰር ምልክቶች
- ለሶስት ሳምንታት ያለማቋረጥ የዘለቀ ሳል
- ለመተንፈስ መቸገር
- የደረት እና ጀርባ ህመም (የሳንባ ካንሰር ሲስፋፋ በአጥንት እና ነርቮች ላይ ጉዳይ ያስከትላል)
- ደም መትፋት
- የመመገብ ፍላጎት መቀነስና ያልተጠበቀ የክብደት መውረድ
- የእጅ ጣቶች የቅርጽ ለውጥ እና የጥፍሮች ማበጥ
- ምግብም ሆነ ፈሳሽ ነገር ለመዋጥ መቸገር
- የድምጽ መሻከር
- ጤናማ ያልሆነ አተነፋፈስ (ትንፋሽ የመብዛት)
ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች የሌሎች በሽታዎችም ምልክት ሊሆኑ ቢችሉም የጤና ባለሙያዎችን ማማከር ሳይታወቅ በሚስፋፋው የሳንባ ካንሰር ህይወትን ከመቀማት ሊታደግ እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የሳንባ ካንሰር የሚያጠቃው ትንባሆ የሚያጨሱትን ብቻ ሳይሆን፥ በሚያጨሱት ዙሪያ ያሉትንም ጭምር በመሆኑ ተገቢውን ምርመራ ማድረግንም ይመክራሉ።