የፍንዳታውን መንስኤ ለማጣራት አምስት ዓቃቤ ህግ መመደቡ ታውቋል
በተርኪዬ ኢስታንቡል ከተማ ኢስቲካልል በሚባለው አውራ ጎዳና ላይ በደረሰ ፍንዳታ በሰዎች ላይ ጉዳት ማስከተሉ ተገለፀ።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በማዕከላዊ ኢስታንቡል በደረሰ ፍንዳታ በትንሹ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ 53 ቆስለዋል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ፍንዳታውን "ጥቃት ነው" ብለውታል።
የኢስታንቡል ገዥ አሊ ዬርሊካያ በቲውተር ገፃቸው በፍንዳታው በመጀመሪያ ሪፖርት መሰረት አራት ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ 38ቱ ደግሞ ቆስለዋል ብለዋል።
በማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ የተጋሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በፍንዳታው ጉዳት ሳቢያ ብዙ ሰዎችን መሬት ላይ ወድቀው ታይተዋል።
የሀገሪቱ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ጠቅላይ ቦርድ በፍንዳታው እና በደረሰው ጉዳት ላይ ሪፖርት ለማድረግ ጊዜያዊ እገዳ ጥሏል። ቀደም ባሉት ጊዜያት ተመሳሳይ ሁኔታዎችን ተከትሎ እንዲህ ዓይነት እገዳዎች ተጥለው እንደነበር ዶቼ ዌሌ ዘግቧል።
ፍንዳታው የደረሰበት የኢስቲካል በርካታ የውጭ ሀገር ነዋሪዎች መኖሪያ እና በጎብኝዎች የሚዘወተር ነውም ተብሏል።
የተርኪዬ መንግስት የዜና ወኪል አናዶሉ እንደዘገበው የፍንዳታውን መንስኤ ለማጣራት አምስት ዓቃቤ ህግ ተመድቧል።
ቀደም ሲል በኢስቲካል በፈረንጆቹ 2016 በአጥፍቶ ጠፊ በደረሰ ፍንዳታ የአራት ሰዎችን ህይወት ሲያልፍ 39 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።