በፍንዳታው የውጭ ሃገራት ተዋጊዎች ጭምር መሞታቸው ተነግሯል
ያጠመዱት ፈንጅ ፈንድቶ ከ60 የሚልቁ የአልሸባብ አባላት መሞታቸውን የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር አስታወቀ፡፡
ጦሩ በደቡባዊ ሶማሊያ ከቁራይሌ ከተማ በስተምዕራብ በ65 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኝ አላ ፉቶው በተሰኘች አንዲት መንደር ባጋጠመው ፍንዳታው የውጭ ሃገራት ቅጥረኞችን ጨምሮ ከ60 በላይ የቡድኑ አባላት መገደላቸውን አስታውቋል፡፡
አላ ፉቶው በታችኛው ሸበሌ ዞን የምትገኝ መንደር ናት፡፡
ፍንዳታውም በዚህችው መንደር በሚገኝ የታጣቂዎቹ መኖሪያ ቅጥረ ግቢ ውስጥ ያጋጠመ ነው፡፡
የቡድኑ የፈንጂ ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎች የውጭ ታጣቂዎችም ተገድለዋ ብሏል ጦሩ፡፡
ከፍንዳታው በኋላ የሃገሪቱ ወታደሮች በአላ ፉቶው ዘመቻ አድርገው የቡድኑን ተሽከርካሪዎች ጨምሮ ሌሎች መገልገያዎቹን ማውደማቸውንም ገልጿል፡፡
ሶማሊያ በተጠናከረ ጸረ-አልሸባብ ዘመቻዎች ላይ ትገኛለች፡፡
ለባለፉት ሶስት ሳምንታት በተካሄዱ ዘመቻዎች ከመቶ የማያንሱ የሽብር ቡድኑን አባላት መግደሏንም ሶማሊያ አስታውቃለች፡፡