በህንድ በሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ አቅራቢያ ፍንዳታ ተከሰተ
እስራኤል “ምንም ጉዳት አላደረሰም” ያለችው ፍንዳታ የጥቃት ሙከራ ሊሆን እንደሚችል ገልጻለች
የህንድ መገናኛ ብዙሃን ፍንዳታው በተከሰተበት አካባቢ ለእስራኤል አምባሳደር የተጻፈ ደብዳቤ መገኘቱን እየዘገቡ ነው
በኒውደልሂ በሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ አቅራቢያ ምሽት ላይ ፍንዳታ መሰማቱ ተነግሯል።
የህንድ ፖሊስ ጥቆማው ደርሶት በአካባቢው ተገኝቶ ምርመራ መጀመሩ የተነገረ ሲሆን፥ ፍንዳታው በኤምባሲው ሰራተኞች ላይ ጉዳት አላደረሰም ብለዋል የኤምባሲው ቃል አቀባይ ጉይ ኒር።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ፍንዳታው የጥቃት ሙከራ ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል።
ይህም የምርመራ ስራው ሲጠናቀቅ ይፋ ይደረጋል ያለችው ቴል አቪቭ በህንድ የሚገኙ ዜጎቿ እንዲረጋጉ ጠይቃለች።
እስራኤል በሃማስ ላይ ጦርነት ካወጀች በኋላ በተለያዩ ሀገራት ሊፈጸሙ የሚችሉ የጸረሴማዊ ጥቃቶችን ለማስቆም በተጠንቀቅ ላይ ነች ተብሏል።
የኒው ደልሂው ፍንዳታ በማን እንደተፈጸመና ምን አላማ እንዳለው እስካሁን አልታወቀም።
የህንድ ፖሊስ ሶስት ስአት ከወሰደ ምርመራ በኋላም የደረሰበት ነገር እንደሌለና ኤምባሲውም ተከፍቶ ስራውን መቀጠሉን ነው ሬውተርስ ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ የዘገበው።
የህንድ መገናኛ ብዙሃን ግን ፍንዳታው በተከሰተበት ስፍራ ለእስራኤል አምባሳደር የተጻፈ ደብዳቤ መገኘቱን እየዘገቡ ነው።
ኢንዲያን ኤክስፕረስ በኮምፒውተር የተጻፈው መልዕክት አምባሳደሩን የሚሳደብና ዛቻ የተሞላበት ነው ብሏል።
የህንድ ፖሊስ እያደረገው በሚገኘው ምርመራም ፍንዳታውና የተገኘው ደብዳቤ ግንኙነት እንዳላቸው ለማረጋገጥ ጥረቱን ቀጥሏል ተብሏል።
በጥር ወር 2021ም በኒው ደልሂ በሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ አቅራቢያ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።
ቴል አቪቭ የሽብር ጥቃት ነው ያለችው ፍንዳታ ምንም ጉዳት ባያደርስም ኤምባሲዋ ኢላማ መደረጉ እንዳሳሰባት መግለጿም አይዘነጋም።