ከእስራኤል የተነሳው አውሮፕላን በሩሲያ ዳጌስታን አውሮፕላን ማረፊያ ምን ገጠመው?
በመቶዎች የሚቆጠሩ የፍልስጤምን ሰንደቅ አላማን የያዙ የእስራኤል ተቃዋሚዎች አውሮፕላኑን ከበው ሲያስጨንቁ አምሽተዋል
የሩሲያ ፖሊስ ከ60 በላይ ተቃዋሚዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል
በሩሲያ ዳጌስታን ክልል የሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ትናንት ምሽት በመቶዎች በሚቆጠሩ የእስርኤል ተቃዋሚዎች ተሞልቶ እንደነበር ተገልጿል።
ተቃዋሚዎቹ በዳጌስታን አውሮፕላን ማረፊያ የፍልስጤምን ሰንደቅ ይዘው እስራኤልን ሲቃወሙ የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
መነሻውን እስራኤል ያደረገ አውሮፕላን ማረፉን ተከትሎ ተቃዋሚዎቹ አውሮፕላኑን ከበው ብጥብጥ ለመፍጠር መሞከራቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የጸጥታ ሃይሎች ደርሰው ግርግሩን ከማረጋጋታቸው በፊትም 20 ሰዎች መቂሰላቸው ነው የተነገረው።
በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት እስራኤላውያን ግን ጉዳት አልደረሰባቸውም ተብሏል።
በሩሲያ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኙና ሙስሊሞች በሚበዙባቸው አካባቢዎች እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት የሚቃወሙ ሰልፎች በተደጋጋሚ እየተካሄዱ ነው።
በካባርዲኖ ባልካሪያ ክልል እየተገነባ የነበረ የአይሁዳውያን ማዕከል ከሰሞኑ በተቃዋሚዎች መቃጠሉ ይታወሳል።
የሩሲያ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር በምሽቱ የዳጌስታን አውሮፕላን ማረፊያ ተቃውሞ ተሳትፎ ያደረጉ ከ150 በላይ ሰዎችን ማንነት መለየቱንና እስካሁን 60 የሚጠጉ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
የዳጌስታን ክልል አስተዳዳሪ ሰርጌ ሜሊኮቭም ተቃዋሚዎቹ ለፍልስጤማውያን ንጹሃን ድምጽ ለመሆን ቢጥሩም የመረጡት ስፍራ እና ህግን የጣሰ አካሄድን መከተላቸው ተገቢ አይደለም በሚል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
እስራኤል የሩሲያ ባለስልጣናት ዜጎቿን ከመሰል ተቃውሞ እና ሁከት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርባለች።
የፍልስጤም ነጻ ሀገር ሆና መመስረትን የምትደግፈው ሩሲያ በጋዛ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ከሁለቱም ወገኖች ጋር ንግግር እያደረገች ነው።
ከሰሞኑ የሃማስ ልኡካንን ወደ ሞስኮ መጋበዟ ግን ቴል አቪቭን ማስቆጣቱ አይዘነጋም።