ብሊንከን ከጋዛው ጦርነት ወዲህ 11ኛ የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸውን ጀመሩ
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተቋረጠውን የጋዛ ተኩስ አቁም ድርድር ለማስጀመር እስራኤል ገብተዋል
ሚኒስትሩ ለአንድ ሳምንት በሚዘልቀው የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸው ወደ ዮርዳኖስና ኳታርም ያቀናሉ
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እስራኤል ገቡ።
ሚኒስትሩ ቴል አቪቭ የገቡት ሄዝቦላህ ወደ ማዕከላዊ እስራኤል በርካታ ሮኬቶችን ከተኮሰ ከስአታት በኋላ ነው።
ብሊንከን የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ 11ኛ የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸው ሲሆን፥ በእስራኤል ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁና ከመከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት ጋር ይመክራሉ።
እስራኤል በጋዛ እና በሊባኖስ በኢራን ይደገፋሉ በሚባሉ ቡድኖች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እያደረሰች በምትገኝበት ወቅት የጀመሩት ጉብኝትም የተቋረጠውን የጋዛ ተኩስ አቁም ድርድር ማስጀመር ያለመ መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል።
10 ጊዜ በእስራኤልና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በመጓዝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥረት ያደረጉት ብሊንከን 11ኛው ጉዟቸውም የተሳካ ውጤት ይታይበታል ተብሎ አይጠበቅም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተደጋጋሚና ያልተሳካ ጉዞም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውድቀት ማሳያ ተደርጎ ሲነሳ ቆይቷል።
ከእስራኤል ባሻገር በዮርዳኖስ እና ኳታር ቆይታ የሚያደርጉት ዲፕሎማት በአሁኑ ጉዟቸው ግን ተጨባጭ ውጤት ያመጡ ዘንድ ይጠበቃል።
ከሁለት ሳምንት በኋላ ከሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አስቀድሞ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ካልተደረሰ ለዴሞክራቷ ካማላ ሃሪስ ፈታኝ እንደሚሆን ነው ተንታኞች የሚያነሱት።
የጋዛውን ጦርነት ማስቆም ሳትችል በሊባኖስ ከሄዝቦላህ ጋር ውጊያ መጀመሩ የኔታንያሁ አስተዳደር ከ17 ቢሊየን ዶላር በላይ ወታደራዊ ድጋፍ ከፈቀደለት የባይደን መንግስት ጋር ተደጋጋሚ ቅራኔ ውስጥ ገብቷል።
በቅርቡም እስራኤል በጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይደርስ የምታደርገውን እገዳ በ30 ቀናት ውስጥ ካላቆመች ወታደራዊ ድጋፉ ሊቋረጥ እንደሚችል ብሊንከንና የመከላከያ ሚኒስትሩ ሊዩድ ኦስቲን በደብዳቤ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።
ቴል አቪቭ በሊባኖስ መዲና ቤሩትና ሌሎች ከተሞች ላይ እየፈጸመችው ያለው የአየር ድብደባ በንጹሃን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን በመግለጽም ጥንቃቄ እንድታደርግ አስጠንቅቀው ነበር።
የኔታንያሁ አስተዳደር ግን የእስራኤል የደህንነት ስጋት ናቸው፤ ከኢራን አፍራሽ ተልዕኮ ወስደው እያጠቁን ነው በሚላቸው የፍልስጤሙ ሃማስ እና የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ላይ ጥቃቱን አጠናክሯል።
ሄዝቦላህ ዛሬ ማለዳ በቴል አቪቭ አቅራቢያ የሚገኝ ወታደራዊ ጣቢያ እና በሃይፋ በስተምስራቅ የሚገኝ የባህር ሃይልን ኢላማ ያደረጉ የሮኬት ጥቃቶችን መፈጸሙን ገልጿል።