እስራኤል ለኢራን ሲሰራ ነበር ያለችውን የስለላ መረብ መበጠሷን የእስራኤል የጸጥታ ኃይል አስታወቀ
የእስራኤል ፖሊስ እንደገለጸው ይህ ወንጀል ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ከተፈጸሙት ውስጥ ከባድ የሚባል ነው
ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ለገንዘብ ብለው "የእስራኤልን መንግስት እና ዜጎች ጎድተዋል"ብሏል
እስራኤል ለኢራን ሲሰራ ነበር ያለችውን የስለላ መረብ መበጠሷን የእስራኤል የጸጥታ ኃይል አስታወቀ።
የእስራኤል የጸጥታ ኃይል ለኢራን ደህንነት መረጃ ሲሰበስብ ነበር ያለውን የስለላ መረብ መበጣጠሱን የእስራኤል ሺን ቤት እና ፖሊስ በዛሬው አስታውቀዋል።
ሽን ቤት እና ፖሊስ ባወጡት የጋራ መግለጫ እንዳስታወቁት ከወደብ ከተማዋ ሀይፋ ጨምሮ ከሰሜን እስራኤል ሰባት እስራኤላውያን የእስራኤል ወታደራዊ ሰፈሮች፣ የኃይል እና የወደብ መሰረተልማቶችን የተመለከቱ መረጃዎችን መሰብሰባቸው በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ ታስረዋል።
የእስራኤል ፖሊስ እንደገለጸው ይህ ወንጀል ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ከተፈጸሙት ውስጥ ከባድ የሚባል ነው።
"ግምገማው የስለላ ቡድኑ አባላት ተግባር በሀገሪቱ ደህንነት ላይ ጉዳት እያስከተሉ መሆኑን የሚያሳይ ነው"ሲሉ የሺን ቤት ጸጥታ አገልግሎት ምንጭ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሁለት ታዳጊዎችን ያካተተው በስለላ የተጠረጠረው ቡድኑ በሁለት የኢራን ኤጀንቶች በሀገሪቱ የጦር ሰፈሮች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስራዎችን እንዲሰራ ታዞ እንደነበር የጋራ መግለጫው ጠቅሷል።
መግለጫው እንዳለው በሰሜናዊቷ ሀደራ ከተማ የሚገኘው የኃይል ጣቢያ፣ የጦር ሰፈሮች በተለይም የአየር ኃይል እና የባህር ኃይል፣ የእስራኤል የአይሮንዶም የአየር መከላከያ ባትሪ እና ወደቦች ኢላማ ከተደረጉት ውስጥ ናቸው።
ተጠርጣሪዎቹ ይህን ስራ የሰሩት በምትኩ በክሪፕቶከረንሲ በመቶሺዎች የሚቅጠር ዶላር ለማግኘት ነው።
ከፍተኛ የሽን ቤት ምንጭ እንዳሉት "የተያዙት አብዛኞቹ ቁሳቁሶች በስለላ ቡድኑ የተሰበሰቡ እና ለኢራን ኤጀንቶች ተላልፈው የተሰጡ ናቸው።"
ተጠርጣሪዎቹ ለገንዘብ ብለው "የእስራኤልን መንግስት እና ዜጎች ጎድተዋል"ብሏል ፖሊስ። ክሱ በእስራኤል አቃቤ ህግ ቢሮ በሚቀጥሉት ቀናት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ባለፈው መስከረም ወር የእስራኤል የደህንነት አገልግሎት ከኢራን ተልእኮ ተቀብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁን ጨምሮ ተዋጊ ሰዎችን ለመግደል አሲሯል ብሎ የጠረጠረውን እስራኤልዊ ማሰሩ ይታወሳል።
እስራኤል በኢራን ውስጥ የስለላ ስራ በመስራት ለረጅም ጊዜ ሰሟ የሚነሳ ሲሆን ባለፈው ሀምሌ ወር የሀማስ የፖለቲካ መሪ የሆነውን እስማኤል ሀኒየህን ቴህራን ውስጥ በመግደል ተጠርጥራለች። እስራኤል ለዚህ ግድያ ኃላፊነት አልወሰደችም።