ባለጸጋ እስራኤላዊያን በሐማስ የታገቱ ዜጎችን ለሚለቁ የገንዘብ ጉርሻ ማዘጋጀታቸውን ገለጹ
ባለጸጋዎቹ ለአንድ ታጋች እስራኤላዊ 100 ሺህ ዶላር እንደሚከፍሉ ተናግረዋል
በአሜሪካ የሚኖሩ እስራኤላዊንም 10 ሚሊዮን ዶላር ለማዋጣት በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል
ባለጸጋ እስራኤላዊያን በሐማስ የታገቱ ዜጎችን ለሚለቁ የገንዘብ ጉርሻ ማዘጋጀታቸውን ገለጹ፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት በመካከለኛው ምስራቅ የተጀመረው ጦርነት መቋጫ ያላገኘ ሲሆን በየዕለቱ አዳዲስ ክስተቶችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡
ሐማስ በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ሲያደርስ 251 ዜጎችን አግቶ ወስዷል የተባለ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 97ቱ አሁንም በሐማስ እጅ ስር እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
የእስራኤል ጦር ታጋቾቹን ለማስለቀቅ በጋዛ ድብደባ ሲያደርግ አንድ ዓመት ያለፈው ሲሆን እስራኤላዊያንም በተለያዩ መንገዶች ታጋቾች እንዲለቀቁ ጫና በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ከእስካሁኑ በተለየ መንገድ እስራኤላዊን ባለጸጋዎች ታጋቾችን ለሚለቁ የገንዘብ ስጦታ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የእስራኤል የጦር ካቢኔ በኢራን ላይ ስለሚሰነዘረው ጥቃት ለምን ሳይስማማ ቀረ?
ዳንኤል ብረንቡም የተባሉት ከአልኮል ነጻ መጠጥ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ከታገቱበት በህይወት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ላደረጉ አጋቾች 100 ሺህ ዶላር እንደሚሰጡ መናገራቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ባለጸጋው ገንዘቡን በካሽ አልያም በቢትኮይን መልክ እከፍላለሁ ያሉ ሲሆን እስካሁን ከ100 በላይ ስልክ እንደተደወለላቸው ተናግረዋል፡፡
ከ100 ሺህ ደዋዮች ውስጥ አብዛኛው የሹፈት ስልኮች ሲሆኑ ከ20 እስከ 30 የሚሆኑት ግን ትክክለኛ ደዋዮች መሆናቸውን ተከትሎ ጉዳዩን ለእስራኤል መንግስት አሳውቄያለሁም ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በአሜሪካ የሚኖሩ ሌሎች እስራኤላዊን ታጋቾችን ለሚለቁ ሰዎች በተመሳሳይ የገንዘብ ማዋጣት መጀመራቸው ተገልጿል፡፡
ባለጸጋዎቹ 10 ሚሊዮን ዶላር ለማዋጣት እንቅስቀሴ መጀመራቸውን የተናገሩ ሲሆን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ከ400 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ተሰብስቧል ተብሏል፡፡
አንድ ኣመት ባለፈው ጦርነት ከ1 ሺህ 200 በላይ እስራኤላዊን ሲገደሉ ከ42 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊን ደግሞ ተገድለዋል፡፡
እስራኤል የሐማሱን መሪ ያህያ ሲንዋርን መግደሏን ተከትሎ የተኩስ አቁም ሊደረግ ይችላል በእገታ ላይ ያሉ እስራኤላዊያንም ሊለቀቁ ይችላሉ የሚል ተስፋ እየጨመረ መጥቷል፡፡