ፔንታጎን እስራኤል በቤሩት የምትፈጽመውን ድብደባ እንድትቀንስ ጠየቀ
የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ሊዩድ ኦስቲን በንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ”እጅግ ከፍተኛ ነው” ብለዋል
በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ሊባኖሳውያን ቁጥር 2 ሺህ 448 ደርሷል
ፔንታጎን እስራኤል በሊባኖስ መዲና ቤሩት እና በከተማዋ ዙሪያ የምትፈጽመውን ድብደባ እንድትቀንስ ጥሪ አቀረበ።
በንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ ነው ያሉት የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ሊዩድ ኦስቲን፥ ፤ በእስራኤል እና ሊባኖስ ድንበር የተፈናቀሉ ሰዎች እንዲመለሱ ድርድር ሊጀመር ይገባል ብለዋል።
እስራኤል በትናንትናው እለት በቤሩት ደቡባዊ ክፍል የሄዝቦላህ የመሳሪያ ማከማቻን መደብደቧን አስታውቃለች።
የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 2 ሺህ 448 መድረሱንና ከ11 ሺህ 500 በላይ መቁሰላቸውን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
“የንጹሃን ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው” ያሉት የፔንታጎን መሪ ሊዩድ ኦስቲንም በጉዳዩ ዙሪያ ከእስራኤሉ አቻቸው ዮቭ ጋላንት ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።
በቡድን 7 አባል ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትር ስብሰባ በጣሊያኗ ኔፕልስ የሚገኙት ኦስቲን፥ እስራኤል በሊባኖስ ከሚገኘው የመንግስታቱ ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ (UNIFIL) ጋር ስለገባችው ሰጣ ገባም ከጋላንት ጋር መምከራቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የሰላም ማስከበር ተልዕኮው ባለፈው ሳምንት የእስራኤል ወታደሮች በተደጋጋሚ “ሆን ብለው” ጥቃት አድርሰውብኛል፤ የተወሰኑ ወታደሮችም ቆስለዋል ማለቱ የሚታወስ ነው።
የእስራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር ግን ሀገራቸው በሰላም አስከባሪዎች ላይ ጥቃት የመሰንዘር የተለየ ፍላጎትና ግብ እንደሌላት ነግረውኛል ብለዋል ሊዩድ ኦስቲን።
እስራኤል ከሶስት ሳምንት በፊት በደቡባዊ ሊባኖስ እግረኛ ጦሯን አስገብታ ከሄዝቦላህ ጋር እያደረገችው የምትገኘው ውጊያ እና በቤሩትና አካባቢው የምትፈጽመው የአየር ጥቃት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል።
ሄዝቦላህም በየቀኑ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን መተኮሱን የቀጠለ ሲሆን፥ በትናንትናው እለትም የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ቤት ኢላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።
ኔታንያሁ ቤታቸው ከተመታ በኋላ በሰጡት አስተያየት “የኢራን ተላላኪ ከሆኑ አሸባሪዎች ጋር የምናደርገውን ውጊያ ቀጥለናል፤ ከማሸነፍ የሚያቆመን ነገር የለም” ብለዋል።
የእስራኤል ዋነኛ አጋር አሜሪካ ቴል አቪቭ በጋዛ እና ሊባኖሱ ጦርነት የንጹሃንን ጉዳት እንድትቀንስና የሰብአዊ ድጋፍ በስፋት እንዲገባ እንድትፈቅድ ደጋግማ ጠይቃለች።
ባለፈው ሳምንትም የመከላከያ ሚኒስትሩ ሊዩድ ኦስቲን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን የፈረሙበት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለእስራኤል መላኩን የሬውተርስ ዘገባ አውስቷል።
ደብዳቤው እስራኤል በ30 ቀናት ውስጥ ሰብአዊ ድጋፍ ወደ ጋዛ በብዛት እንዲገባ ካልፈቀደች ዋሽንግተን ወታደራዊ ድጋፏን ልትቀንስ እንደምትችል የሚያስጠነቅቅ ነበር።
ተንታኞች ግን ማስጠንቀቂያው የይስሙላ ነው ይላሉ። በጋዛ የደረሰውን ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ማስቆም ያልቻለችው/ያልፈለገችው አሜሪካ በሊባኖስም ተመሳሳይ አቋም እያሳየች መሆኑንም ይገልጻሉ።