እስራኤል የሀማስ የመጨረሻ ምሽግ ይገኝባታል የምትላትን ራፋን ለማጥቃት በቀጣይ ሳምንት ንጹሀንን ልታስወጣ ነው ተባለ
እስራኤል የሀማስ የመጨረሻ ምሽግች የሚገኙት በራፋ ስለሆነ ራፋን ማጥቃት ሀማስን ሙሉ በሙሉ ለመደምስስ አስፈላጊ ነው ብላ ታምናለች
እስራኤል ከራፋ ለሚወጡ ሰዎች መጠለያ የሚሆን በ10ሺዎች የሚቆጠር ድምኳን መግዛቷ ተዘግቧል
እስራኤል የሀማስ የመጨረሻ ምሽግ ይገኝባታል የምትላትን ራፋን ለማጥቃት በቀጣይ ሳምንት ንጹሀንን ልታስወጣ ነው ተባለ።
እስራኤል የሀማስ የመጨረሻ ምሽግ ይገኝባታል የምትላትን የራፋ ከተማ ለማጥቃት በሚቀጥለው ሳምንት ንጹሃንን ማስወጣት እንደምትጀሞር ተገልጿል።
እስራኤል ከራፋ ለሚወጡ ሰዎች መጠለያ የሚሆን በ10ሺዎች የሚቆጠር ድምኳን መግዛቷን ሮይተርስ የእስራኤል ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
በግብጽ ድንበር የምትገኘው የጋዛ ከተማ ግማሽ አመት በሆነው የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ሸሽተው በመጡ ተፈናቃዮች ተጨናንቃለች። ይህ የእስራኤል ራፋን የማጥቃት እቅድ የስደተኛ ማዕበል ሊከሰት ይችላል የምትለውን ግብጽን እና ምዕራባውያን ስጋት ውስጥ ከቷል።
በንጹሀን ጥበቃ ጉዳይ ከአሜሪካ መንግስት ጋር ለሳምንታት ውይይት ከተካሄደ በኋላ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር እያንዳንዳቸው ከ10-12 ሰዎች ማስጠለል የሚችሉ 40,000 ድንኳኖችን መግዛቱን ዘገባው ጠቅሷል።
በኢንተርኔት የተሰራጨ ቪዲዮ ከራፋ በአምስት ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ካን ዮኒስ ነጭ ድንኳኖች ተደርድረው ያሳያል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የጦር ካቢኔት የንጹሀን ማስወጣትን ስራ ለማስጀመር በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ይሰበሰባል ተብሏል።
እስራኤል በራፋ ከተማ ጥቃት እንዳታደርስ የእስራኤል እና ሀማስ አደራዳሪዎች ግብጽ፣ ኳታር እና አሜሪካ ጫና ቢያደርጉም፣ እስራኤል የማጥቃት እቅዷን አልቀለበሰችም።
እስራኤል የሀማስ የመጨረሻ ምሽግች የሚገኙት በራፋ ስለሆነ ራፋን ማጥቃት ሀማስን ሙሉ በሙሉ ለመደምስስ አስፈላጊ ነው ብላ ታምናለች።
ባለፈው ጥቅምት ወር ሀማስ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ እየወሰደችው ባለው መጠነሰፊ የአየር እና የምድር ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ34ሺ በላይ አልፏል።