በእስራኤል ሃማስ ጦርነት የሞቱ ፍሊስጤማውያን ቁጥር ከ34 ሺህ አልፏል
እስራኤል በዱባበዊ ጋዛ ከተማ በምትገኘው ራፋህ ሌሊቱን በፈጸመችው ጥቃት 22 ሰዎች መሞታቸውን የፍሊስጤም ጤና ሚኒስቴር ባለስልጣናት አስታወቁ።
በእስራኤል አየር ጥቃት ከሞቱት መካከል ስድቱ ሴቶች ሲሆኑ፤ አምስቱ ህጻናት ናቸው፤ ከህጻናቱ መካከልም ከተወለደ ገና 5 ቀኑ የሆነ ጨቅላ ህጻን ይገኘበታል ተብሏል።
እስራኤል ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ በራፋህ በተከታታይ የአየር ድብደባዎችን ስትፈጽም የቆየች ሲሆን፤ ራፋህ የሃማስ ጠንካራ ይዞታ ነው ብላ እንደምታምንም ስትገልጽ ቆይታለች።
በሚሊየን የሚቆጠሩ ፍሊስጤማውያን ጦርነቱን ሸሽተው ከግብጽ ጋር በምትወዋሰነው ጋዛ ተጠልለው እንደሚገኙም ነው የሚታወቀው።
ይሁን እንጂ እስራኤል የሃማስ ጠንካራ ይዞታ ነው ብላ ወደምታምነው ወደ ራፋህ እግረኛ ጦር እንደምታስገባም እየዛተች ትገኛለች።
አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በበኩላቸው እስራኤል ወደ ራፋህ እግረኛ ጦር ከማስገባት እንድትቆጠብ በማሳሰብ ላይ ይገኛሉ።
የፍሊስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት መሃሙድ አባስ በትናንትናው እለት፤ “እስራኤል እግረኛ ጦሯን እንዳታስገባ ማስቆም የምትችለው ብቸኛ ሀገር አሜሪካ” ነች በማለት፤ አሜሪካ እስራኤልን እንድተስቆም ጠይቀዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም የእስራኤል ሃመስ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ለ7ኛ ጊዜ ወደ መካከለኛ ምስራቅ ያቀኑ ሲሆን፤ በሳዑዲ አረቢያ፣ ጆርዳን እና እስራኤል በጦርነቱ ዙሪያ ከባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ ተብሏል።
የእስራኤል ሃማስ ጦርት ከስድስት ወራት በፊት ጥቅምት 7 የሃማስን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ የተቀሰቀሰ ሲሆን፤ ሃማስ በወቅቱ ባደረሰው ድንገተኛ ጥቃት 1 ሺህ 200 እስራኤላውያንን መግደሉ እና 250 ገደማ ሰዎችን አግቶ መውደሱ ይታወሳል።
እስራኤል የሃማስን ጥቃት ተከትሎ በጋዛ በከፈተችው ጥቃትም እስካሁን የተገደሉ ፍሊስጤማውያን ቁጥር ከ34 ሺህ የተሸገረ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ሁለት ሶስተኛው ህጻናት እና ሴቶች ናቸው።