ብሊንከን የሩሲያ ጥቃት ባየለበት ወቅት በባቡር ኬቭ ገብተዋል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉዞ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገው ድጋፍ እንደሚቀጥል ለማሳየት ያለመ ነው ተብሏል
ሩሲያ በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን አዲስ ጥቃት በመክፈት ከተሞችን መቆጣጠሯን ማስታወቋ ይታወሳል
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ኬቭ ገብተዋል።
ብሊንከን የአሜሪካ ኮንግረንስ ለዩክሬን የ61 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ካጸደቀ በኋላ በኬቭ ጉብኝት ያደረጉ የመጀመሪያው ከፍተኛ የዋይትሃውስ ባለስልጣን ሆነዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሚስጢራዊውን ጉብኝት ለማድረግ ከፖላንድ ወደ ኬቭ በባቡር ማቅናታቸው ተዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሚያዚያ ወር ያጸደቁት የተተኳሽ ጥይቶች፣ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚስኤሎች እና የአየር መቃወሚያዎች ኬቭ መድረሳቸው ተገልጿል።
ይሁን እንጂ ዩክሬን የምዕራባውያኑ ድጋፍ በፍጥነት ባለመድረሱ የመልሶ ማጥቃት መጀመር እንዳልቻለችና ሩሲያም በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን ጥቃቷን ማጠናከሯን ስትገልጽ ቆይታለች።
ሞስኮ ከሰሞኑም በካርኪቭ አቅራቢያ የምትገኝ ከተማን መቆጣጠሯን ማስታወቋ ይታወሳል።
የዩክሬንን 18 በመቶ መሬት በቁጥጥር ስር ያዋለችው ሩሲያ ለሁለት አመት በምስራቅና ደቡባዊ ዩክሬን ስታካሂደው የቆየችውን ጦርነት አሁን ወደ ሰሜኑም አስፋፍታለች።
ይህም ለኬቭ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን የሚያነሳው ሬውተርስ የብሊንከን ጉብኝትም ለኬቭ በሚላኩ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች ላይ ትኩረት ያደርጋል ብሏል።
የአሜሪካ ብሄራዊ የደህንነት አማካሪው ጃክ ሱሊቫኒ በትናንትናው እለት ዋሽንግተን ወደ ኬቭ የምትልከውን የጦር መሳሪያ “በብዛትና በፍጥነት” ለማድረስ እየሰራች ነው ማለታቸው ይታወሳል።
የመሳሪያ ድጋፉ ከፍተኛ ክፍተት መፍጠሩን በማመንም በዚህ ሳምንት አዲስ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ይፋ እንደሚሆን አብራርተዋል።
የሩሲያ ጦር በበኩሉ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ቢያንስ ዘጠኝ መንደሮች እና አነስተኛ ከተሞችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
ሞስኮ ከሰሞኑ በዩክሬን እያስመዘገበችው ያለው ድል ጦርነቱ ከተጀመረ ከየካቲት 2022 ወዲህ ፈጣኑና ስኬታማው ነው ተብሏል።