የጀርመኑ የሊዮፓርድ ታንክ አምራች ትርፋማነቱ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ገለጸ
የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ለኩባንያው ትርፋማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ተብሏል
የሊዮፓርድ ታንክ አምራች ኩባንያ የፈረንጆቹ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ትርፍ የ60 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል
የጀርመኑ የሊዮፓርድ ታንክ አምራች ራሂንሜታል ኩባንያ ትርፋማነቱ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለጸ።
የሊዮፓርድ ታንክ አምራቹ ራሂንሜታል ኩባንያ በፈረንቹ 2024 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ትርፍ በ60 በመቶ መጨመሩን ዛሬ ባወጣው ሪፖርቱ አስታውቋል።
ራሂንሜታል ኩባንያ ትርፋማነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውም የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ እንደሆነም ተነግሯል።
የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎም የጀርመኑ የራሂንሜታል ኩባንያ የገበያ ዋጋ ከአራት እጥፍ በላይ ማደጉም ነው የተገለጸው።
ራሂንሜታል ኩባንያ ዩክሬን ጦርነት ተከትሎ ለኪቭ መንግስት የሊዮፓርድ ታንኮችን ለማቅረብ ከምእራባውያን ሀገራት ከፍተኛ የሆነ ትእዛዞችን እየተቀበለ መቆየቱም ተነግሯል።
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ አርሚን ፓፐርገር በመግለጫው ላይ "በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የጦር መሳሪያዎች ፍላጎት ለማርካት የራሂንሜታል ኩባያ ተፈላጊነት በበርካታ ሀገራት እየጨመረ ነው" ብለዋል።
የሊዮፓርድ ታንክ አምራቹ ራሂንሜታል ኩባንያ በሩብ ዓመቱ የ1.58 ቢሊየን ዩሮ ጦር መሳሪያ ሽያጭ በማካሄድ 134 ሚሊየን ዩሮ ትርፍ ማግኘቱ ተነግሯል።
ከጥር እስከ መጋቢት ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ የኩባያው የጦር መሳሪያ የሽያጭ መጠን ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ16 በመቶ ከፍ ብሏል።
ጀርመን ምዕራባውያን ካሏቸው ታንኮች የሚስተካከለው የለም የሚባልለትን ሊዮፓርድ ወደ ዩክሬን መላኳ ይታወሳል።
ጀርመን ሰራሹ ሊዮፓርድ ታንክ በምዕራቡ አለም ሁነኛ የጦር መሳሪያ ተደርጎ ይወሰዳል።
የጀርመን መከላከያ ሃይል ተቋም ራሂንሜታል ኩባንያ ከፈረንጆቹ 1978 ጀምሮ ከ3 ሺህ 500 በላይ ሊዮፓርድ ታንኮችን አምርቷል።
ከ60 ቶን በላይ የሚመዝነውና በናፍጣ የሚሰራው ታንክ እስከ 5 ኪሎሜትር ትክክለኛ ኢላማውን መምታት ይችላል። ፖላንድ፣ ኖርዌይ፣ ስፔን፣ ስዊድን እና ቱርክን ጨምሮ 20 ሀገራት ይህን ታንክ ይጠቀሙበታል።