የሩሲያ ጦር በዩክሬኗ በካርኪቭ ከተማ አቅራቢያ የምትገኝ የድንብር ከተማ ተቆጣጠረ
ካርኪቭ በሰሜን ምስራቅ የምትገኝ ሁለተኛዋ ግዙፍ የዩክሬን ከተማ ነች
ዩክሬን በአካባቢው አሁንም ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው ብላለች
ሩሲያ ወታደሮቿ ዩክሬኗ ሁለተኛ ግዙፍ ከተማ ካርኪቭን በሰሜን ምስራቅ በኩል የምታዋስነውን ቮቭቻንስክ የተባለች ከተማ መቆጣጡን አስታወቀች።
ቮቭቻንስክ አነስተኛ ከተማ ከዩክሬን ሁለተኛዋ ግዙፍ ከተማ ካርኪቭ በ75 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትግኝ አነስተኛ ከተማ መሆኗም ተነግሯል።
ሩሲያ ካሳለፍነው ሳምንት አርብ ጀምሮ በዩክሬን የምትፈጽምን ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ማጠናከሯን ተከትሎ ጦሯ ባለፉት ቀናት ውስጥ ቢያስ 9 መንደሮችን እና አነስተኛ ከተሞችን መያዝ እንደቻለ ተነግሯል።
የሩሲያ ጦር ከሰሞኑ እያስመዘገበ ያለው ድል ጦርነቱ ከተጀመረ ከፈረንጆቹ 2022 ወዲህ ከፍተኛው እንደሆነም ነው የተነገረው።
የሩሰያ ጦር ቮቭቻንስክ አነስተኛ ከተማ መያዙን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ወደ ካርኪቭ እየሸሹ መሆኑ ተነግሯል።
የዩክሬን ጦር በጉዳዩ ላይ በሰጠው ማብራሪያ፤ ሩሲያ እስከ አምስት ሻለቃ ማሰማራቷነ በመግለጽ፤ ሩሲያ እንደ አዲስ አጠናክራ በቀጠለችው ጥቃት ታክቲካዊ ስኬት እንዳገኘች አምኗል።
ነገር ግን የሩሲያ በየቀኑ ከ100 በላይ ወታደሮችን በጦር ግንባር እያጣች መሆኑንም የዩክሬን ጦር አስታውቋል።
በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር የዋለችው ቮቭቻንስክ አነስተኛ ከተማ ብዙም ወታደራዊ ጠቀሜታ የሌላት ቢሆንም በዩክሬናውያን ሞራል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል ተብሏል።
የካርኪቭ አስተዳዳሪ ኦሌህ ሳይኔሁቦቭ፤ ሩሲያ ጥቃቅን ቡድኖችን በመጠቀም ሆን ብላ ጦር ግንባሩን ለማስፋት እየጣረች ነው ብለዋል።
የዩክሬን ጦር የሩሲያን ወታሮች ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ እያደረጉ ነው ያሉት አስተደዳሪው፤ ግጭሩ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ሊስፋፋ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ በሳለፍነው ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ፤ በስትሪሌቻ እና ፕሌቴኒቭካ እንዲሁም በክራስኔ፣ ሞሮኮቬትስ፣ ኦሊኒኮቭ፣ ሉኪንቺ እና ሃቲሽቼ በተባሉ መንደሮች ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንደቀጠለ ነው ብለዋል።
“ወታደሮቻችን በጦር ግንባሮቹ የዩክሬናውያንን ድንብር ለማስጠበቅ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ እየወሰዱ ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ።
ሩሲያ ካሳለፍነው የካቲት ወር ወዲህ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትሰነዝረውን ጥቃት አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፤ ዩክሬን በበኩሏ የምእራባውያ የጦር መሳሪያ ድጋፍ በወቅቱ አለመደረሱ ሩሲያ በጦር ግንባር የበላይ እንድትሆን እያደረጋት ነው ብላለች።
የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ጄነራል ኦሌክሳንደር ሰርሰይኪ ከሳምንት በፊት በጦር ግንባር ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን መግለጻቸው ይታወሳል።
ዩክሬን ቁልፍ ወታደራዊ ስፍራዎችን ማጣቷን ያመኑት ዋና አዛዡ፤ ሞስኮ በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ ታክቲካዊ ስኬትን አስመዝግባለች ብለዋል።
ጄነራል ኦሌክሳንደር ሰርሰይኪ አክለውም ዩክሬን ጦር የሚያስፈለግውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከአሜሪካ ከማግኘቱ በፊት ሩሲያ ያላትን የወታደርና የጦር መሳሪያ ቁጥር ብላጫ በመጠቀም ቦታዎችን እየተቆጣጠረች መሆኑን አስታውቀዋል።