አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የ400 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ ይፋ አደረገች
አሜሪካ ይህን ድጋፍ ያደረገችው ሩሲያ በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን ካርኪቭ ግዛት አዲስ የውጊያ ግንባር በመክፈት ወደ ዩክሬን ግዛት የተወሰነ ቦታ መግፋቷን ተከትሎ ነው
የአሜሪካ የተወካዮች ምክርቤት ለዩክሬን የ61 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ አጽድቋል
አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የ400 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ ይፋ አደረገች።
የአሜሪካ የተወካዮች ምክርቤት የ95 ቢሊዮን ወታደራዊ እርዳታ ካጸደቀ በኋላ ለዩክሬን በመደበኛነት የጦር መሳሪያ ማቅረብ የጀመረችው አሜሪካ፣ ተጨማሪ የ400 ሚሊዮን ዶላር ወታራዊ እርዳታ ለማቅረብ መዘጋጀቷን ኃይትሀውስ በትናንትናው እለት አስታውቋል።
ከጸደቀው የ95 ቢሊዮን ወታደራዊ እርዳታ ውስጥ 61 ቢሊዮን ዶላሩ ለዩክሬን እንደሚሰጥ መገለጹ ይታወሳል።
የእርዳታ ማዕቀፉ ከባድ መሳሪያን፣ ለናሳምስ የአየር መከላከያ ሚሳይል የሚሆን ተተኳሽን፣ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን እና በጦር ግንባር ጥቅም ላይ የሚውሉ ትናንሽ መሳሪያዎችን እንደሚያካትት ሮይተርስ አንድ የአሜሪካ ባለስልጣንን ጠቅሶ ዘግቧል።
የጦር መሳሪያ እርዳታውን የተወካዮች ምክርቤት ማጽደቅ ሳያስፈልግ በፕሬዝደንሻል ዳውንዋርድ ኦቶሪቲ(ፒዲኤ) ትዕዛዝ ከአሜሪካ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት በአስቸኳይ እንዲተላለፍ ይደረጋል ተብሏል።
አሜሪካ ይህን ድጋፍ ያደረገችው ሩሲያ በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን ካርኪቭ ግዛት አዲስ የውጊያ ግንባር በመክፈት ወደ ዩክሬን ግዛት የተወሰነ ቦታ መግፋቷን ተከትሎ ነው።
የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት ተባብሶ ሲቀጥል፣ የአሜሪካ የመከላከያ ኩባንያዎች ተጨማሪ ለማምረት ብዙ ኮንትራት ያገኛሉ።
እንደ ሎክሂድ ማርቲን፣ ጀነራል ዳይናሚክስ እና ኖርዝሮፕ ጎሩማን የመሳሰሉት መሳሪያ ለማምረት ከአሜሪካ መንግስት የመከላከያ ኮንትራት ከሚያስሩ ኩባንያዎች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ዩክሬን በሩሲያ የተያዘውን የአየር የበላይነት ለመቀልበስ ያስችላታል የተባለውን አሜሪካ ሰራሽ ኤፍ-16 የጦር ጄት ከሰኔ እስከ ሐምሌ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ እጇ እንደምታስገባ ገልጻለች።