የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ እስራኤል አቀኑ
በሃማስ እና እስራኤል ጦር ግጭት 22 አሜሪካውያን ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፥ በሃማስ ከታገቱት ውስጥም አሜሪካውያን ይገኙበታል
የአንቶኒ ብሊንከን ጉብኝት ዋሽንግተን ለቴልአቪቭ ያላትን ድጋፍ የምታሳይበት ነው ተብሏል
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በእስራኤልና ዮርዳኖስ ጉብኝት ለማድረግ ጉዞ ጀምረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ “በአጭር እና ግልጽ ቋንቋ አሜሪካ የእስራኤል አጋር ናት” ብለዋል።
ብሊንከን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ግጭቱ በሚቆምበት ሁኔታ እንደሚመክሩ ሬውተርስ ዘግቧል።
ከስድስት ቀናት በፊት ሃማስ በእስራኤል ላይ በከፈተው ያልተጠበቀ ጥቃት እና የእስራኤል ጦር በወሰደው የአጻፋ ምላሽ ህይወታቸው ካለፈ 1 ሺህ 200 ሰዎች ውስጥ 22ቱ አሜሪካውያን ናቸው።
በሀማስ ከታገቱ ከ100 በላይ ሰዎች ውስጥም አሜሪካውያን እንደሚገኙበት ነው የተገለጸው።
አንቶኒ ብሊንከን በእስራኤል ቆይታቸው የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ ጥረት ያደርጋሉ የተባለ ሲሆን፥ ከፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አባስ ጋር በዮርዳኖስ እንደሚመክሩ ሲጂቲኤን ዘግቧል።
አሜሪካ ከትናንት በስቲያ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ወደ እስራኤል መላኳ ይታወሳል።
አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከቧንም ወደ እስራኤል ማስጠጋቷ የፍልስጤሙ ሃማስ እና የእስራኤልን ግጭት እንዳያባብሰው ተሰግቷል።
ዋይትሃውስ መርከቧን ያስጠጋነው በቀጠናው ያሉ ሌሎች ታጣቂ ሃይሎች በግጭቱ እጃቸውን እንዳያስገቡ ለማድረግ ነው ቢልም ቱርክ በተቃራኒው ግጭቱን የሚያባብስ ነው በሚል ተቃውማዋለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን በእስራኤል ቆይታቸው እንደ ሄዝቦላህ ያሉ በኢራን የሚደገፉ ሃይሎች ከሃማስ ጋር እንዳይተባበሩ ጠንከር ያለ መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሏል።
ብሊንከን ከቅዳሜ ጀምሮ ከአረብ ኤምሬትስ፣ ሳኡዲ፣ ግብጽ፣ ቱርክ፣ ኳታርና ዮርናዶስ አቻዎቻቸው ጋር ግጭቱ በሚቆምበት ሁኔታ መክረዋል።
ዋሽንግተን ከእስራኤል ጋር ግንኙነቷን ለማደስ ጥረት እያደረገች ያለችው ሳኡዲ እና ሌሎች የአረብ ሀገራት በሃማስ ላይ ጫና እንዲፈጥሩም እየተንቀሳቀሰች ነው።