ኤርዶጋን የአሜሪካን የጦር መርከብ ወደ ጋዛ የማስጠጋት ውሳኔ ተቹ
ኤርዶጋን ቀደም ሲል እስራኤሌን እና የፍልስጤም ኃይሎችን ለማደራደር ቱርክ ዝግጁ መሆኗን ገልጸው ነበር
አሁን ላይ ሀማስ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን ቢገልጽም እስራኤል ጋዛን በመክበብ ጥቃቷን አጠናክራ ቀጥላለች
የቱርኩ ፕሬዝደንት ኤርዶጋን የአሜሪካን የጦር መርከብ ወደ ጋዛ የማስጠጋት ውሳኔ ተችተዋል።
ፕሬዝደንቱ የአሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከብ ወደ እስራኤል መጠጋት በጋዛ "ከባድ ጭፍጨፋ" እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል በሚል ነው አሜሪካ ላይ ትችት የሰነዘሩት።
ባለፈው ቅዳሜ ሀማስ በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ልልዮድ ኦስቲን አሜሪካ ዩኤስኤስ ጀራልድ አር. ፎርድ የተሰኘችውን ግዙፍ የጦር መርከብ ያካተተ የባህር ኃይል ቡድን ወደ እስራኤል ማስጠጋቷን ተናግረዋል።
"ኤርክራፍት የምትሸከመው የጦር መርከብ እስራኤል አቅራቢያ ምን ትሰራለች፣ ለምን መጣች? ጋዛን እና አካባቢውን በመምታት ከባድ ጭፍጨፋ እንዲደረግ ያደርጋሉ" ሲሉ ኤርዶጋን ከኦስትሪያ ቻንስለር ካርል ኔሃመር ጋር በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ኤርዶጋን ቀደም ሲል እስራኤሌን እና የፍልስጤም ኃይሎችን ለማደራደር ቱርክ ዝግጁ መሆኗን ገልጸው ነበር።
ግጭቱ የተቀሰቀሰው ፍልስጤምን ትደግፍ የነበረችው ቱርክ የሀማስ አባላትን ተቀብላ ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ለአመታት የዘለቀውን በጠላትነት መተያየት ለማስቀረት እየሰራች ባለችበት ወቅት ነው።
ሀማስ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለትን የእስራኤልን ድንበር ጥሶ በመግባት በደቡባዊ እስራኤል ከተሞች ላይ ከባድ ጥቃት ፈጽሟል።
በጥቃቱ ከ1200 በላይ እስራኤላውን ተገድለዋል፤ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቆስለዋል።
የሀማስን ጥቃት ተከትሎ ጦርነት ውስጥ መግባቷን የገለጸችው እስራኤል የሀማስ ይዞታ በሆነችው ጋዛ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መፈጸሟን ቀጥላለች።
በእስራኤል ጥቃት 900 ሰዎች ሲገደሉ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ተሰደዋል።
አሁን ላይ ሀማስ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን ቢገልጽም እስራኤል ጋዛን በመክበብ ጥቃቷን አጠናክራ ቀጥላለች።