የአሜሪካን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች የጫነ አውሮፕላን እስራኤል ደረሰ
የጦር መሳሪያ ድጋፉ እስራኤል ከሃማስ ጋር የእግረኛ ውጊያ እንድትጀምር ያደርጋታል ተብሏል
ዋሽንግተን ግዙፍ የጦር መርከቧንም ወደ እስራኤል ማስጠጋቷ ተነግሯል
ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን የጫነው የአሜሪካ አውሮፕላን ትናንት ምሽት እስራኤል መድረሱ ተነገረ።
በደቡባዊ እስራኤል ኔቫቲም አየር ሃይል ጣቢያ የተራገፈው የጦር መሳሪያ አይነት ምን እንደሆነ በይፋ አልተገለጸም።
የጦር መሳሪያው “(በሃማስ ላይ) ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድና ተጨማሪ ዝግጅት ለማድረግ ያግዛል” ነው ያሉት የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዳኔል ሃጋሪ።
“በዚህ ፈታኝ ወቅት አሜሪካ ላደረገችልን ድጋፍ ምስጋናችን የላቀ ነው” ብለዋል።
እስራኤል ከአሜሪካ ጋር ያላት ወታደራዊ ትብብር መጠናከር የቀጠናውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረውም በማከል።
አሜሪካ በቀጣይም በአውሮፕላኖቿ የጦር መሳሪያዎችን ወደ እስራኤል እንደምትልክ ይጠበቃል።
ይህም እስራኤል በጋዛ ከሃማስ ጋር ፊት ለፊት የእግረኛ ውጊያ ለማድረግ ያስችላታል ነው የተባለው።
አሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ ግዙፍ መርከቧን “ዩኤስኤስ ጀራልድ ፎርድ” ወደ ምስራቃዊ ሜዲትራኒያን ባህር ማስጠጋቷንም አስታውቃለች።
የጦር መርከቧ በሃማስና እስራኤል መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት ሌሎች ሃይላት እጃቸውን እንዳያስገቡ ትከላከላለች ተብሏል።
ይሁን እንጂ እንደ ቱርክ ያሉ ሀገራት አሜሪካ የጦር መርከቧን ወደ እስራኤል ማስጠጋቷን ተቃውመዋል።
ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን የኤሜሪካ የጦር መርከብ ወደ እስራኤል መቅረቧ “በጋዛ ጭፍጨፋ ለመፈጸም ነው እንጂ ለሌላ አይሆንም” ሲሉ የዋይትሃውስን የግጭቱን ተዋናዮች ቁጥር ለመቀነስ ነው አመክንዮ ውድቅ አድርገዋል።
ቱርክ የፍልስጤሙ ሃማስ እና እስራኤልን ለማደራደር ዝግጁ መሆኗንም አስታውቃለች።
ለሃማስ ድጋፍ የነበራት አንካራ ከቴልአቪቭ ጋር ለአመታት ሻክሮ የቆየውን ግንኙነቷን ለማደስ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።