በእስራኤል-ሀማስ ጦርነት ላይ አሜሪካ ጣልቃ ከገባች እስራኤልን እንደሚያጠቁም አማጺያኑ ተናግረዋል
የየመን አማጺያን አሜሪካ በእስራኤል-ሀማስ ጦርነት ጣልቃ እንዳትገባ አስጠነቀቁ፡፡
ባሳለፍነው ቅዳሜ የፍልስጤሙ ሀማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ ጦርነት መከሰቱ ይታወሳል፡፡
በሁለቱ አካላት ጦርነት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸው ሲያልፍ የቆሰሉ እና የታገቱ ዜጎች ቁጥርም በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል፡፡
በርካታ ሀገራት ክስተቱን አስመልክተው የተለያዩ መግለጫዎችን ያወጡ ሲሆን የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር አሜሪካ የሀማስን ጥቃት ካወገዙ ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ናት፡፡
ዋሸንግተን ጥቃቱን ከማውገዝ ባለፈ ለእስራኤል የቀጥታ ድጋፍ እንደምታደርግ የገለጸች ሲሆን በዛሬው ዕለትም የጦር መሳሪያዎችን የጫነው አውሮፕላን እስራኤል ገብቷል፡፡
የአሜሪካን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች የጫነ አውሮፕላን እስራኤል ደረሰ
ይህን ተከትሎም የየመን አማጺያን አሜሪካ በእስራኤል-ሀማስ ጦርነት ጣልቃ እንዳትገባ አስጠንቅቋል፡፡
የየመን ሁቲ አማጺ ቡድን መሪ አብዱል ማሊክ አል ሁቲያ እንዳለው ' አሜሪካ በእስራኤል-ሀማስ ጦርነት ላይ የቀጥታ ተሳትፎን ካደረገች እኛም የድሮን እና ሚሳኤል ጥቃት በእስራኤል ላይ እንሰነዝራለን ብሏል፡፡
ሀማስን ለመርዳት ጥቃት እንደሚሰነዝሩ የተናገሩት አማጺያኑ አሜሪካ ጣልቃ እንዳትገባ አስጠንቅቀዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ እስራኤል የሀማስ ታጣቂዎች እና መገልገያዎች ናቸው ባለቻቸው የጋዛ ሰርጥ ቦታዎች ላይ የአየር እና የየብስ ጥቃቶችን በማድረስ ላይ መሆኗን አስታውቃለች፡፡
ከ2 ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማዊያን ይኖሩበታል የሚባለው ጋዛ ሙሉ ለሙሉ በእስራኤል የተዘጋ ሲሆን ምግ፣ ውሃ እና ነዳጅ አቅርቦትም እንደተቋረጠ ተገልጿል፡፡