ብሊንከን በጋዛ ታጋቾች ጉዳይ ከአል ሲሲ ጋር ለመወያየት ካይሮ ገቡ
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን በጋዛ ታጋቾች ጉዳይ ለመምከር በዛሬው እለት ካይሮ ገብተዋል
ይህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት የእስራኤል እና ሀማስ ግጭት ከተጀመረበት ከባለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ አምስተኛ ጊዜ የተካሄደ ነው
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን በጋዛ ታጋቾች ጉዳይ ለመምከር በዛሬው እለት ካይሮ ገብተዋል።
ብሊንከን በካይሮ የግብጹን ፕሬዝደንት አብደል ፋታህ አል ሲሲን በማግኘት ኳታር እና ግብጽ የሚያደርጉትን የተኩስ አቁም እና የታጋቾች መለቀቅ ድርድር እንዲያፋጥኑ ጫና እንደሚያደርጉ ሮይተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካው ዋና ዲፕሎማት ብሊንከን ወደ ካይሮ ያቀኑት ከሳኡዲ አረቢያ ጉብኝት በኋላ ነው።
ይህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት የእስራኤል እና ሀማስ ግጭት ከተጀመረበት ከባለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ አምስተኛ ጊዜ የተካሄደ ነው።
አሜሪካ በጋዛ ያለው ተኩስ መቆም ታጋቾች እንዲለቀቁ ለማድረግ እና ለሌሎች ፈተናዎች መፍትሄ ለመስጠት ቁልፍ ነው ብላ ታስባለች።
በጋዛ ያለው ተኩስ ሲቆም የፍልስጤም ሀገርነት ሂደት እንዲፋጠን እና የእስራኤል እና ሳኡዲ አረቢያ ግንኙነት የማደስ ሂደት እንዲጀመር ያስችላል።
እስራኤል በጋዛ ላይ በምታደርገው መጠነሰፊ ጥቃት አጋርነቷን ያሳየችው አሜሪካ፣ በተመድ የጸጥታው ምክርቤት የቀረበውን የተኩስ አቁም የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።
አሜሪካ በኢራን ይደገፋሉ በሚባሉት እና ለፍለስጤሙ ሀማስ አጋርነት ባሳዩት የሀውቲ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ እየወሰደች ነው።
የሀውቲ ታጣቂዎች ወደ እስራኤል በሚያመሩ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረስ ከጀመሩ በኋላ አሜሪካ በእነሱ ላይ እርምጃ እየወሰደች ትገኛለች።
በቅርቡ የአሜሪካ ወታደሮች ጆርዳን ውስጥ መገደላቸውን ተከትሎ አሜሪካ በኢራቅ እና በሶሪያ ባሉ የኢራን ኢላማዎች ላይ ድብደባ አካሂዳለች።