የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ለ8ኛ ጊዜ ወደ አረብ ሀገራት የሚያቀኑት ብሊንከን ጉዞ ለምን ስኬታማ አልሆነም?
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ባይደን ያቀረቡትን የተኩስ አቁም ስምምነት ሀማስ እንዲቀበል ለማግባባት ከነገ በስቲያ ወደ አረብ ሀገራት ያቀናሉ
ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ለ8ተኛ ግዜ የሚደረገው የብሊንከን ጉዞ ውጤታማነት ከአሁኑ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል
የአሜካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በመጪው ሰኞ ለ8ተኛ ግዜ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ያቀናሉ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ በዚህኛው ጉብኝታቸው የአረብ ሀገራት ፕሬዝደንት ጆባይደን ያቀረቡትን የተኩስ አቁም ስምምነት ሀማስ እንዲቀበል ከአረብ ሀገራት ጋር ይመክራሉ ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በፈረንሳይ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት ባይደን ጋር በፓሪስ የሚገኙት ቢሊንከን በመጪው ሰኞ ወደ ግብጽ ካይሮ የሚያቀኑ ሲሆን እስራኤል፣ ጆርዳን እና ኳታር ቀጣይ መዳረሻዎቻቸው ናቸው፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ሚንስትሩ በጉብኝታቸው ከሀገራቱ መሪዎች ጋር በሚኖራቸው ቆይታ ጦርነቱን ለማስቆም ስምምነቱ የሚኖረው ሚና ላይ ይመክራሉ ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ሀማስ ስምምነቱን እንዲቀበል ሀገራቱ በማግባባቱ ረገድ በሚኖራቸው ሃላፊነት ላይ እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል፡፡
ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው በመመለስ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር እና ሰብአዊ ድጋፎችን ያለገደብ ለማዳረስ ያግዛል የተባለው ስምምነት ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም ወሳኝ በመሆኑ በሁለቱ ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ዋሽንግተን እየጠየቀች ትገኛለች፡፡
በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ሲጥሩ ከነበሩ የኳታር የመንግስት ሀላፊዎች ጋር የሚገናኙት ብሊንከን የአረብ ሀገራት በሀማስ ላይ ያላቸውን ተጽእኖ በማስተባበር ረገድ ከሀላፊዎቹ ጋር እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በእስራኤል በሚኖራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር የሚገናኙ ሲሆን እየበረታ ስለሚገኝው አለም አቀፋዊ ተጽእኖ እና እስራኤል ጦርነቱን ለመቋጨት ይህን ስምምነት እንድትቀበል ጠቅላይ ሚንስትሩን ያግባባሉ ተብሏል፡፡
ሆኖም ከኔታንያሁ ጋር የሚኖራቸው ቆይታ ፍሬያማነት ላይ ብዙዎች ስጋት አላቸው። እስራኤል የአሜሪካን የተኩስ አቁም ስምምነት ጥያቄ በበጎ እንደምትመለከተው ብትገልጽም እስካሁን በይፋ እሽታዋን አልገለጸችም፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ስምመነት ከተቀበሉ እና ጦርነቱን ካቆሙ መንግስታቸውን እንደሚያፈርሱ የሚዝቱ ቀኝ ዘመም የእስራኤል ፓርቲዎችን ሀሳብ ማስለወጥ የብሊንከን ተጨማሪ የቤት ስራ ሊሆን ይችላል፡፡
ሀማስ በበኩሉ ስምምነቱን ሊቀበል የሚችለው እስራኤል በዘላቂ የተኩስ አቁም ላይ ከተስማማች እና በቅድሚያ ጦሯን ከጋዛ ካስወጣች ብቻ ነው ብሏል፡፡
በዚህ መካከል እውን ለመሆን በርካታ ፈተናዎች ያሉበት ስምምነት ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ነው የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ወደ አረብ ሀገራት የሚያቀኑት፡፡
በ8ወራቱ ጦርነት በወር አንድ ግዜ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የተጓዙት አንቶኒ ብሊንከን ይዘዋቸው በተጓዙት ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎች ውጤታማ መሆን አልቻሉም በሚል ይተቻሉ፡፡
እስራኤል በሲቪልያን ላይ የምታደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ጥንቃቄ እንድታደርግ ለማሳሰብ ፣ የተኩስ አቁሞች እንዲደረጉ ለማግባባት እና በተጋቾች ልውውጥ ዙርያ በአረብ ሀገራት እንዲሁም በእስራኤል ያደረጉት ጉብኝት እምብዛም ውጤታማ አለነበረም፡፡
አሁን ደግሞ ለ8ተኛ ግዜ የጆ ባይደንን የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ ወደ ቀጠናው ይጓዛሉ።
ባይደን በ2024ቱ ምርጫ ለማሸነፍ የጋዛውን ጦርነት ማስቆም ወሳኝ ካርድ ነው፡፡ በጦርነቱ ዙርያ የሚሰበሰቡ የህዝብ አስተያየቶችም ይህንኑ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡