የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ ግለሰብ ተመቱ
የአውሮፓ ህብረት ኃላፊ ቻርለስ ሚሼል እና የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝደንት ሮቤርታ ሜሶላ በፍሬድሪክሰን ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል
የዴንማርኳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቲ ፍሬዲሪክሰን በትናንትናው እለት በኮፐንሀገን አደባባይ ጥቃት እንደደረሰባቸው ጽ/ቤታቸው አስታወቀ
የዴንማርኳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቲ ፍሬዲሪክሰን በትናንትናው እለት በኮፐንሀገን አደባባይ ጥቃት እንደደረሰባቸው ጽ/ ቤታቸው ማስታወቁን ቪኦኤ ዘግቧል።
የአውሮፓ ህብረት ኃላፊ ጥቃቱን ወዲያውኑ አውግዘታል። ፍሬድሪክሰን በጥቃቱ መደንገጣቸውን ለኤኤፍፒ በሰጠው መግለጫ የገለጸው የጠቅላይ ሚኒስትሯ ጽ/ቤት ተጨማሪ ማብራሪያ አልረጠም።
"ጠቅላይ ሚኒስትሯ ትናንት ምሽት በኮፐንሀገን ኩልቶረቬት በአንድ ግለሰብ ተመትተዋል። ድርጊቱን የፈጸመው ወዲያው ተይዟል" ብሏል ጽ/ቤቱ።
ይህ ጥቃት በስራ ወይም በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ባሉ ፓለቲከኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ተከታታይ ጥቃት ተከትሎ የተፈጸመ ነው። በግንቦት ወር አጋማሽ የስሎቫክ ጠቅላይ ሚነስትር በማዕከላዊቷ የሀንድሎቫ ከተማ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ሰላምታ እየሰጡ ባለበት ወቅት አራት ጊዜ በጥይት ተመተው ቆስለዋል።
ፊኮ ከጥቃቱ በኋላ ወደ ሆስፒታል ተወስደው ረዘም ላለ ጊዜ ህክምና ተደርጎላቸው መዳን ችለዋል።
የአውሮፓ ህብረት ኃላፊ ቻርለስ ሚሼል እና የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝደንት ሮቤርታ ሜሶላ በፍሬድሪክሰን ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል።
"ጥቃት በፓለቲካ ቦታ የለውም" ያሉት ሚሶላ የዴንማርክ መንግስት እንዲጠነክር በኤክሰ ገጻቸው ጽፈዋል።
ሚሼል በበኩላቸው በጥቃቱ መናደዳቸውን ተናግረዋል።"ይህን የፈሪዎች ጥቃት በጽኑ አውግዛለሁ" ብለዋል የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዝደንት በኤክስ ገጻቸው።
በጠቅላይ ሚኒስተሯ ላይ ጥቃት መድረሱን ያረጋገጠው የኮፐንሀገን ፓሊስ ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጠም።
"ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አንድ ሰው ይዘን ምርመራ እያካሄድን ነው። አሁን ላይ ተጨማሪ አስተያየትም ሆነ መግለጫ የለንም" ብሏል ፓሊስ በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ።