ጉብኝቱ በአሜሪካ እና ቻይና መካከል የተካረረውን ልዩነት ለማርገብ እንደሚያግዝ ታምኖበታል
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለሁለት ቀናት ጉብኝት ቻይና ገብተዋል።
ብሊንከን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ዋይትሃውስ ከዘለቁ ወዲህ ቻይናን የረገጡ የመጀመሪያው የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ሆነዋል።
በየካቲት ወር ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት የቻይና ተንሳፋፊ ፊኛዎች በአሜሪካ መታየታቸውን ተከትሎ ያራዘሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ በቆይታቸው ከቻይና አቻቸው ሺን ካንግ ጋር ይመክራሉ ተብሏል።
ብሊንከን ከቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋርም ሊወያዩ እንደሚችሉ ይገመታል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
የብሊንከን ጉብኝት በቀጣይ ወራት የግምጃ ቤት ሃላፊዋን ጃኔት የለን እና የንግድ ሚኒስትሯን ጂና ሬይሞንዶ የቤጂንግ ጉዞ እንደሚያቃና ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግም 2023 ማጠናቀቂያ ላይ ፊት ለፊት እንዲመክሩ ሁኔታዎችን ያመቻቻል ነው የተባለው።
ሁለቱ መሪዎች በህዳር ወር በኢንዶኔዥያዋ ባሊ ያደረጉት ምክክር የሀገራቱን ውጥረት ማርገቡ የሚታወስ ነው።
የቻይና ተንሳፋፊ ፊኛዎች በአሜሪካ ሰማይ ላይ ከታዩ በኋላ ግን በሁለቱም ሀገራት በኩል ዲፕሎማሲያዊ ንግግሩ መዳከሙ ይነገራል።
ሃያላኑ ሀገራት አሁንም በታይዋን ጉዳይ፣ በደቡባዊ ቻይና ባህር ቅኝት እና በሌሎች ቀጠናዊ ጉዳዮች ሰጣ ገባቸው በየጊዜው እየተባባሰ ነው፤ የንግድ ማዕቀቦችም ቀጥለዋል።
የአንቶኒ ብሊንከን ጉብኝትም የከረረው እንዳይበጠስ ያለመ መሆኑ ተነግሯል።
ሁለቱም ሀገራት በከፍተኛ ባለስልጣን ደረጃ ለመነጋገር ዝግጁነታቸውን ማሳየታቸውንም ሚኒስትሩ መናገራቸውን ሬውተርስ አስነብቧል።
የዋይትሃውስ ባለስልጣናት ከብሊንከን ጉብኝት ሰበር ዜና አትጠብቁ ስለማለታቸውም አክሏል።