ቪፒኤን በመጠቀም ቻይናዊያን ይህን አፕ መጠቀም መጀመራቸው ተገልጿል
በኦፕን አይ ኩባንያ የለማው ቻትጂፒቲ ማቀላጠፊያ ወይም አፕ የአርቲፊሺያል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አዳዲስ አገልግሎቶችን ይዞ ብቅ ማለቱ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ይህ መተግበሪያ ለዓለማችን ሰዎች አዳዲስ አገልግሎቶችን ይዞ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን በተለይም የጽሁፍ መልዕክቶችን በመቅረጽ በኩል እጅግ ፈጣን አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ይህ አፕ ግጥምና ዘፈኖችን በአጭር ሰከንድ ውስጥ እንደሚሰራ የተገለጸ ሲሆን ጎግልን ከጥቅም ውጪ ሊያደርገው እንደሚችል ተጠቅሷል።
አዲሱ አፕ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ያፈራ ሲሆን ከሌሎች ተመሳሳይ አፖች ጋር በሚጣጣም መልኩ መሰራቱም ተገልጿል።
ይሁንና ቻይና ይህ አሜሪካ ሰራሽ ኩባንያ በሀገሯ ጥቅም ላይ እንዳይውል ያገደች ሲሆን መተግበሪያው ዜጎችን ለሀሰተኛ መረጃ፣ ለሴራ ትንተና እና ለሌሎች ጉዳቶች ያጋልጣል ብላለች፡፡
በተለይም ግዙፍ የቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ቻትጅፒቲ መተግበሪያን እንዳይጠቀሙ ያስጠነቀቀች ሲሆን ይህን አሜሪካ ሰራሽ አፕ የሚመስል ቻይናዊያን ቢሰሩ የተሸለ እንደሚሆን መታዘዛቸውን የሀገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡
ይሁንና ቪፒኤን መተግበሪያዎችን በመጠቀም በርካታ ቻይናዊያን ቻትጅፒቲ መተግበሪያን እየተጠቀሙ ሲሆን የሀገሪቱ መንግስት ግን ዜጎች እንዳይጠቀሙ ማሳሰቡ ተገልጿል፡፡
የትዊተር ባለቤቱ ኢለን መስክ ከቻትጅፒቲ ኩባንያ መስራቾች መካከል አንዱ ናቸው የተባለ ሲሆን ይህ አፕ ለጥያቄዎች ምላሽ መስጠት፣ የተሳሳቱ መላምቶችን ማረምና ስህተቶችን በመለየት ተወዳጅነትን አግኝቷል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ይህ አፕ የገበያ ጽሁፎችን፣ የምስጋና ደብዳቤ እና ሌሎች ጽሁፎችን በራሱ እንደሚጽፍ ተገልጿል።
ይህ አፕ በተለይም የበይነ መረብ ሽያጭ ስራዎችን፣ መልዕክቶችን፣ ለደንበኞች ምላሽ መስጠት እና ሌሎች የማይገመቱ ተያያዥ አገልግሎቶችን ይሰጣል ተብሏል።