ቻይና ከአሜሪካ ጋር አልወያይም ማለቷ ዋሽንግተንን ማሳሰቡ ተገለጸ
የአሜሪካ መከላከያ አዛዥ ከቻይና አቻቸው ጋር መወያየት ቢፈልጉም ቤጂንግ ፈቃደኛ አልሆነችም
በእስያ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የጸጥታ እና ደህንነት ጉባኤ በሲንጋፖር እየተካሄደ ነው
ቻይና ከአሜሪካ ጋር አልወያይም ማለቷ ዋሽንግተንን ማሳሰቡ ተገለጸ።
በእስያ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እና የተለያዩ ሀገራት መከላከያ እና ሌሎች የደህንነት ተቋማት የተሳተፉበት ጉባኤ በሲንጋፖር በመካሄድ ላይ ነው።
በዚህ ጉባኤ ላይ የአሜሪካ እና ቻይና ወታደራዊ አዛዦች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ የፔንታጎን ዋና አዛዥ ኦስቲን ከቻይና አቻቸው ጋር በተደጋጋሚ መወያየት ቢፈልጉም አልተሳካላቸውም ተብሏል።
ኦስቲን ለሮይተርስ እንዳሉት "ከቻይና ጦር አዛዥ ጋር መወያየት እንደምፈልግ በተደጋጋሚ ብገልጽም ፈቃደኛ አልሆኑም፣ ይህ በጣም ያሳስባል" ብለዋል።
"የበለጠ በተቀራረብን እና በተነጋገርን መጠን አለመግባባቶቻችን እየተፈቱ ይሄዳሉ ብዬ አምናለሁ" ያሉት አዛዡ አለመነጋገራችን ወደ ግጭት እና ቀውስ ሊወስደን ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ጠቅሰዋል።
የቻይና ወታደራዊ አዛዥ ሊ ሻንግፉ ከአሜሪካ አቻቸው ጋር የመነጋገር ፍላጎት እንደሌላቸው በተደጋጋሚ አስታውቀዋል።
ከቻይና ወታዱራዊ አዛዦች መካከል እንዱ የሆኑት ሌተናንት ጀነራል ጂንግ ጂያንፌንግ ቤጂንግ የደቡባዊ ቻይና ባህርንም ሆነ የታይዋንም ጉዳይ በራሷ መፍታት እንደምትችል ታምናለች ሲሉ ተናግረዋል ።
የቻይና እና አሜሪካ ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ ዝቅተኛ መተማመን ደረጃ ላይ ደርሷል የተባለ ሲሆን የታይዋን ጉዳይ፣ የደቡባዊ ቻይና ባህር፣ የዩክሬን ጦርነት እና ማዕቀቦች ለግንኙነታቸው መበላሸት ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው።
አሜሪካ ከኢንዶ ፓስፊክ ሀገራት ጋር በመቀናጀት ከቻይና ጎረቤት ሀገራት ጋር የበለጠ ግንኙነቷን እያጠበቀች ሲሆን ይህ ደግሞ ቤጂንግን አላስደሰተም።
የሁለቱ የዓለማችን ሀያላን ሀገራት አለመግባባት ዳፋው ለዓለም እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የበለጠ የተሸረሸረው የቀድሞ የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን ከጎበኙ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።