ቻይና አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጣልኩ ያለችውን ማዕቀብ ተቃወመች
ፕሬዝዳንት ባይደን በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ ማእቀብ እንዲጣል የቀረበላቸውን የውሳኔ ሃሳብ በፊርማቸው ማጽደቃቸው የሚታወስ ነው
ቤጂንግ የጉዳዩ ባለቤቶች ችግሩን የመፍታት ብልሃቱ አላቸው ብላለች
በኢትዮጵያ ተፈጽሟል ካለችው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ አሜሪካ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል መወሰኗን ቻይና ተቃወመች።
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊጂያን ዣኦ አሜሪካ ጠንቃቃ እና አርቆ አሳቢ ከመሆንም በላይ ገንቢ ሚናን እንደምትጫወት ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።
የሚመለከታቸው አካላት ልዩነቱን በወጉ ለመፍታት፣ ብሔራዊ እርቅ ለማምጣት እና ወደ ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ የሚችሉበት ብልሃትና ችሎታ እንዳላቸው እናምናለንም ነው ቃል አቀባዩ ያሉት።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ተፈጽሟል ከሚሉት የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ማእቀብ መጣል እንዲቻል የቀረበላቸውን የውሳኔ ሃሳብ ባሳለፍነው አርብ መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ/ም በፊርማቸው ማጽደቃቸው የሚታወስ ነው።
ማዕቀቡ በዋናነት ጥሰቶቹ እንዲፈጸሙ እና ወደ ስምምነት እንዳይመጣ አድርገዋል ባሏቸው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስት አካላት፣ የህወሓት አመራሮች እና የአማራ ክልል ባለስልጣናናት ላይ የሚጣል ነው እንደ ባይደን አስተዳደር ገለጻ፡፡
አስተዳደሩ ከአሁን ቀደም በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጉዞ እገዳ መጣሉ የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም እገዳው በእነማን ላይ የተጣለ ነው ማንንስ ይመለከታል ስለሚለው የተገለጸ ነገር የለም፡፡
አሜሪካ በኤርትራ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ፍሊጶስ ላይ የሃብት እና የጉዞ እገዳ መጣሏም ይታወሳል፤ ምንም እንኳን የእርምጃው ፍትሐዊነት ተጠየቅ ውስጥ ቢወድቅም ፡፡