ፖለቲካ
"ሉዓላዊነትን እና ግዛታዊ አንድነትን ማክበር ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋትና ልማት አስፈላጊ ነው" - ብሊንከን
ከ4 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ማሻሻላቸውንም አስታውሰዋል
ብሊንከን በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው አዲስ ግጭት የበርካታ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል ብለዋል
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያን "ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት ማክበር ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና ልማት አስፈላጊ ነው" አሉ፡፡
ከአራት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለሁለት አስርት ዓመታት ሻክሮ የቆየ ግንኙነታቸውን ማሻሻላቸውን ያስታወሱት ብሊንከን ሆኖም በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው አዲስ ግጭት የበርካታ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል ብለዋል።
በመሆኑም ከመቼውም ጊዜ በላይ፤ ሉዓላዊነትን እና ግዛታዊ አንድነት ማክበር፤ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት፡፡
ይህ ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና ልማት አስፈላጊ እንደሆነም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
የፌዴራል መንግስት እና የህወሓት ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ደጋግማ ስጠይቅ የነበረችው አሜሪካ ለተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ያላትን ድጋፍ መግለጿ ይታወሳል፡፡
ኤርትራን በጣልቃ ገብነት ስትከስ መቆየቷ የሚታወስም ሲሆን የሃገሪቱን ወታደራዊ ባለስልጣናት ጨምሮ በሌሎች ላይ ማዕቀቦችን መጣሏም አይዘነጋም፡፡