የኢትዮጵያ ተፈላሚ ኃይሎች ግጭቱን በዘላቂነት ወደሚያቆም ውይይት እንዲሸጋገሩ አሜሪካ ጠየቀች
ሚኒስትሩ፤ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ ስራ እንዲጀምሩም ጥሪ አቅርበዋል
ብሊንከን፤ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ በመደበኛነት ለማድረስ የታየውን መሻሻል አድንቀዋል
የሰብዓዊ እርዳታ በማዳረስ ረገድ እየታየ ያለው ለውጥ አሜሪካ በበጎ የምትቀበለው መሆኑን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በመስሪያ ቤታቸው በኩል በሰጡት መግለጫ “ባለፉት ሰባት ቀናት ከ1 ሺህ 100 በላይ ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ትግራይ ደርሷል”ብለዋል፡፡
ትግራይ ክልል ከደረሰው ሰብዓዊ እርዳታ ውስጥ በተመጣጠነ ምግብ እጦት የተጎዱ ሰዎችን ለማከም የሚያስፈልጉ ግብዓቶች፣ የህክምና አቅርቦቶች እና ሌሎች አስፈላጊ እርዳታዎች እንደሚገኙበት በመግለጫው ሰፍሯል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወደ ጦርነት የገቡ አካላትን ለማስታረቅ ጠየቀች
አንቶኒ ብሊንከን በዚሁ መግለጫቸው በአፋር፣ አማራ እና በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ በመደበኛነት ለማድረስ የታየውን መሻሻል ያደነቁ ሲሆን፤ እርዳታው እንዲደርስ በማመቻቸት ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የአፋር እና የትግራይ ከልሎች ባለስልጣናትን “በተለይ” አመስግነዋል።
ተመድ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የአሜሪካ መንግስት አጋሮች እና የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች ሚናም የሚደነቅ መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ ተፈላሚ ኃይሎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ለተቸገሩ በማድረስ ረገድ ያሳዩትን መሻሻል፤ ግጭቱን በዘላቂነት ወደሚያቆም ውይይት እንዲያሸጋግሩት ሲሉም የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጠይቋል፡፡
ብሊንከን በትናንቱ መግለጫቸው በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ ስራ እንዲጀምሩም ጥሪ አቅርበዋል።
በጦርነቱ ወቅት በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የፈጸሙ አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ሀገራቸው እንደምትሻም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አንስተዋል።