በጋዛው የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ 90 በመቶ መግባባት ላይ መደረሱን ብሊንከን ገለጹ
እስራኤል እና ሀማስ ልዩነታቸውን በማጥበብ ስምምነቱን እንዲያጠቃልሉ ሚንስትሩ ጠይቀዋል
ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው የሚንስትሩ ንግግር ትክክለኛ አይደለም ሲሉ አጣጥለዋል
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በጋዛው የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ 90 በመቶ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ሀማስ እና እስራኤል ያልተስማሙባቸው ነጥቦች ጦርነቱን ከማስቆም እና ስምምነት ላይ ከመድረስ የሚያግዱ አይደሉም ብለዋል፡፡
ሁለቱ ተዋጊዎች ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ ስምምነቱን እንዲያጠቃልሉ የጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ስምምነቱ ሳይፈረም አንድ ቀን ባለፈ ቁጥር የተፈጻሚነቱን ውጤታማነት እድል እየቀነሰው ይገኛል ነው ያሉት፡፡
አንቶኒ ብሊንከን በትላንትናው እለት በሄይቲ የነበራቸውን ይፋዊ ጉብኝት ካጠናቀቁ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እስራኤል ጦሯ እንዲቆይ በምትፈልግባቸው የድንበር ስፍራዎች ላይ ሁለቱ አካላት ያለቸውን ልዩነት የሚያጠቡ ከሆነ ስምምነቱ እውን የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው ብለዋል
በተጨማሪም በመጪዎቹ ቀናት ከኳታር እና ግብጽ ጋር በመሆን ቀሪ ጉዳዮችን መፍታት የሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦችን ለሁለቱ ተዋጊዎች እንደሚያቀርቡ ነው የተናገሩት፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው የብሊንከን ንግግር ትክክለኛ አይደለም በሚል አጣጥለውታል፡፡
በትላንትናው እለት ከፎክስ ኒውስ ጋር ቃለመጠይቅ ያደረጉት ጠቅላይ ሚንስትሩ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ በተናገሩት መጠን ለስምምነት የቀረበ ድርድር አልተካሄደም ብለዋል፡፡
ኔታንያሁ ፊላዴልፊያ ከተባለው 14 ኪሎሜትር በሚረዝመው የጋዛ ሰርጥን ከግብጽ ጋር ከሚያዋስነው ድንበር ወታደሮችን አላስወጣም በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በሰየሟቸው የእስራኤል ተደራዳሪዎች እና በአሜሪካ ጭምር ስምምነት ላይ እንዳደረስ ዋና እንቅፋት ከሆነው ከዚህ አቋማቸው እንዲለሳለሱ ቢጠየቁም አሁንም የመለሳለስ አዝማሚያ አላሳዩም፡፡
ሃማስ በበኩሉ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ምድር ሙሉለሙሉ ለቆ የማይወጣ ከሆነ የተኩስአቁም ስምምነቱን እንደማይፈርም በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡
በዚህ ሳምንት ቱርክ እና አምስት የአረብ ሀገራት የእስራኤል ጦር በጋዛ ድንበር አካባቢዎች መቆየቱን እንደሚቃወሙ አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በግንቦት ወር ያቀረቡት በሶስት ዙር ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት ሀሳብ በተደጋጋሚ ለድርድር ቢቀርብም ወደ ፍጻሜ መቅረብ ተስኖታል፡፡