ተመድ በሱዳን የሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲሰማራ ጠየቀ
ድርጅቱ በሁለቱም ተዋጊዎች የሚፈጸሙ የሰበአዊ መብት ጥሰቶች በአስከፊ ሁኔታ እየጨመሩ እንደሚገኙ ገልጿል
በሱዳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ልኡክ በሀገሪቱ በሁለቱም ተዋጊዎች የሚፈጸሙ የሰበአዊ መብት ጥሰቶች ወደ ጦር ወንጀል እያደጉ ነው ብሏል
ተመድ በሱዳን የሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲሰማራ ጠየቀ።
ወሲባዊ ባርነትን ጨምሮ ሌሎች የመብት ጥሰቶች በሁለቱም አካላት እየተፈጸሙ ነው ያለው ተመድ በንጹሀን ላይ የሚደርሱ በደሎችን ለመቀነስ ገለልተኛ የሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲገባ ጠይቋል፡፡
የዘፈቀደ እስር፣ አስገድዶ መድፈር፣ አካላዊ ማሰቃየት፣ ግድያ እና ወሲባዊ ባርነትን ጨምሪ ሌሎችም ወንጀሎች እየተፈጸሙ መሆኑን በሱዳን የተመድ ልኡክ አደረኩት ባለው ጥናት እንደደረሰበት ነው የገለጸው፡፡
ጦርነቱ በተጀመረ የመጀመርያው አመት ውስጥ 400 ሴቶች ተገደው እንደተደፈሩ ነገር ግን ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል በሪፖርቱ ያመላከተው ተመድ፤ ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ህጻናትን ለውትድርና እየመለመለ እንደሚገኝ ተደጋጋሚ ጥቆማዎች እንደደረሱት ይፋ አድርጓል፡፡
በጄነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን የሚመራው ጦር እና ጄነራል ሀማዳን ዳጋሎ የሚያዙት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በእነኚህ ድርጊቶች ላይ እጃቸው እንዳለበት አረጋግጫለሁ ያለው ተመድ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰብአዊ መብት ጥሰቶቹ ከዚህ በላይ እንዲቀጥሉ መፍቀድ የለበትም ሲል አስታውቋል፡፡
ልዑኩ በንጹሀን ላይ የሚፈጸሙ ጥሰቶች በእዚሁ ከቀጠሉ ወደ ጦር ወንጀል ደረጃ እንደሚቀየሩ ገልጾ በአፋጣኝ ንጹሀንን የሚከላከል ሰላም አስከባሪ ሀይል መግባት ይኖርበታል ብሏል፡፡
በአሜሪካ እና በተለያዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በንጹሀን ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ተደጋጋሚ ክስ የሚቀርብባቸው ሁለቱ ተዋጊዎች እርስ በእርስ ከመወነጃጀል ባለፈ ሀላፊነት ወስደው እንደማያውቁ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በሱዳን የተመድ ልኡክ ሰብሳቢ ሞሀመድ ቻንዲ ኦትማን አለማቀፋዊ ጣልቃገብነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የንጹሀን ሱዳናውያንን ህይወት ለማስቀጠል አሁን አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሱዳን ካሏት 18 ክልሎች መካከል በ14ቱ ጦርነቱ ተስፋፍቷል ያሉት ሰብሳቢው የዜጎች ደህንነት ለአደጋ የመጋለጥ እድሉ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም ሁለቱ ተዋጊዎች የጦር መሳርያ ድጋፍ የሚያገኙባቸውን ምንጮች ማድረቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ተጨማሪ የጦር መሳርያ ማዕቀብ እንዲጣልባቸውም ጠይቀዋል፡፡
የሰላም አስከባሪ ሀይሎች በሌሎች ሀገራት የሚሰማሩት በተመድ የጸጥተው ምክር ቤት ሀሳቡ ቀርቦ ይሁንታን ሲያገኝ ነው፡፡
17 ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት ከሱዳን አጠቃላይ ህዝብ ከግማሽ በላዩን ከቀየው ሲያፈናቅል በሚሊየን የሚቆጠሩትን ደግሞ ለርሀብ አደጋ አጋልጧል፡፡
ባሳለፍነው ወር በአሜሪካ መሪነት በሲውዘርላንድ ጄኔቫ ሁለቱን አካላት ለማደራደር የተደረገው ጥረት ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡