ዩክሬን ምዕራባውያን የሞስኮን "ቀይ መስመሮች" ችላ ብለው በረጅም ርቀት ሚሳይል እንድታጠቃ እንዲፈቅዱላት እየተማጸነች ነው
ሩሲያ ምዕራባውያን ዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳይል እንድትጠቀም የሚፈቅዱላት ከሆነ ሶስተኛው የአለም ጦርነት ይነሳል ስትል ዝታለች
ዘለንስኪ ሩሲያ እንድትደራደር ለማስገደድ፣ በረጅም ርቀት ሚሳይል ጥቃት መፈጸም አስፈላጊ ነው ብለዋል
ዩክሬን ምዕራባውያን የሞስኮን "ቀይ መስመሮች" ችላ ብለው በረጅም ርቀት ሚሳይል እንድታጠቃ እንዲፈቅዱላት እየተማጸነች ነው።
የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ምዕራባውያን ሀገራት የሞስኮን "ቀይ መስመሮች" ወደ ጎን ትተው ኪቭ የረጅም ርቀት ሚሳይሎች ተጠቅማ ሩሲያ ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን እንድትመታ እንዲፈቅዱላት በዛሬው እለት ጠይቀዋል።
ዘለንስኪ ይህን ያሉት ዋሽንግተን ተጨማሪ የ250 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያዎች ለመስጠት ቃል በገባችበት ወቅት ነው።
"ሩሲያ እንድትደራደር ለማስገደድ፣ በተወረረው የዩክሬን መሬት ብቻ ሳይሆን በሩሲያ ግዛት ውስጥ ኢላማ ለመምታት የሚያስችል የረጅም ርቀት ሚሳይል ያስፈልገናል" ብለዋል ዘለንስኪ።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን የኩርስክ ጥቃት ዩክሬን በጦር ሜዳ የበላይነት ለመያዝ ያላትን ተነሳሽነት የሚያሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።"ወራሪው የክሬሚሊን ጦር አሁን ወደ መከላከል ገብቷል" ብለዋል ኦስቲን።
ኦስቲን ዩክሬን ሩሲያን ከግዛቷ እንድታስወጣ ለማድረግ ምዕራባውያን ጥረታቸውን መቀጠላቸውን በአጽንኦት ተናግረዋል።
ዩክሬን ባልተጠበቀ ሁኔታ ድንበር ጥሳ በምዕራብ ሩሲያ ግዛት ውስጥ 1300 ስኩየር ኪሎሜትር ስፋት ያለው ቦታ መቆጣጠር ችላለች። ዩክሬን ይህን ጥቃት የከፈተችው በምዕራብ ዩክሬን የተሰማራው የሩሲያ ኃይል ወደ ኋላ እንዲፈገፍግ ለማድረግ ነበር።
ነገርግን የሩሲያ ኃይሎች በምዕራብ ዩክሬን የሚያደርጉትን ጥቃት በማጠናከር በግንባር ለተሰማራው የዩክሬን ጦር ሎጂስቲክስ ለማቅረብ ወሳኝ የሆነችውን የፖክሮቭስክ ከተማ ለመያዝ እየተቃረቡ ናቸው።
ሞስኮ በዩክሬን ከተሞች እየፈጸመች ባለው መጠነሰፊ ጥቃት በርካታ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን መሰረተልማቶችም ወድመዋል።
ዩክሬን የሞስኮን ጥቃት ለመመከት ምዕራባዊያን የአየር መከላከያ እንዲሰጧት እና የረጅም ርቀት በሩሲያ ግዛት ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን እንድትመታ እንዲፈቅዱላት በተደጋጋሚ በመጠየቅ ላይ ነች።
ሩሲያ ምዕራባውያን ዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳይል እንድትጠቀም የሚፈቅዱላት ከሆነ ሶስተኛው የአለም ጦርነት ይነሳል ስትል ዝታለች።