በሀማስ እና እስራኤል መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የቀረበውን “የማቀራረብያ ሀሳብ” እስራኤል መቀበሏን ገለጸች
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር መክረዋል
ባሳለፍነው ሳምንት በኳታር ተጀምሮ ያለ ስምምነት የተጠናቀቀው ድርድር በዚህ ሳምንት ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል
በሀማስ እና እስራኤል መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የቀረበውን “የማቀራረብያ ሀሳብ” እስራኤል መቀበሏን ገለጸች
በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ለማጥበብ አደራዳሪዎች ያቀረቡትን “የማቀራረብያ ሀሳብ” እስራኤል መቀበሏን የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አስታወቁ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን በትላንትናው እለት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ተወያይተዋል፡፡
“የማቀራረብያ ሀሳብ” (ብሪጂንግ ፕሮፖዛል) በሚል የተጠራው ሰንድ ሁለቱ ወገኖች በተኩስ አቁም እና በታጋቾች ልውውጥ ዙርያ ያልተስማሙባቸውን ሀሳቦች የሚያስታርቅ ነው ተብሏል፡፡
ከኔታንያሁ ጋር ለሁለት ሰአት ተኩል ያህል በጉዳዩ ዙርያ የተነጋገሩት ብሊንከን የጋዛውን ጦርነት ለማስቆም የመጨረሻው እና የተሻለው አማራጭ ይህ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም አሜሪካ እና ሌሎች አደራዳሪዎች ያቀረቡትን ይህን “የማቀራረብያ ሀሳብ” እስራኤል እንደምትቀበለው ኔታንያሁ እንደገለጹላቸው አንስተው ሀማስም ተመሳሳዩን እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ሀሙስ እና አርብ ለሁለት ቀናት በሁለቱ ተፋላሚዎች መካከል የተደረገው ድርድር ያለ አንዳች ስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ዴሞክራቶች የህዳሩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከመድረሱ በፊት የጋዛውን ጦርነት በስምምነት በመቋጨት የሙስሊም እና የአረብ አሜሪካኖችን ድምጽ ማግኝት ይፈልጋሉ፡፡
ይሁንና ባለፉት ጊዜያት በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና እየተባባሰ የሚገኝው ውጥረት በተኩስ አቁም ስምምነቶች ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡
ከዚህ ባለፈ ሀማስ ከበርካታ አመታት ወዲህ በእስራኤል ውስጥ የአጥፍቶ ጠፊ የቦንብ ጥቃት መጀመሩን እሁድ ለተፈጸመው ጥቃት ሀላፊነት በወሰደበት ወቅት አስታውቋል፡፡
ይህን ተከትሎም እስራኤል በትላንትናው እለት በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት 30 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
ምንም እንኳን ዋሽንግተን ድርድሩ ጥሩ እርምጃ እየታየበት እንደሆነ ብትገልጽ ሀማስ እና እስራኤል የሚያሳዩት ምልክቶች በድርድሩ ተስፋ እንደሌላቸው የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ድርድሩ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ከአጃንስ ፍራንስ ፕረስ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የሀማስ ከፍተኛ አመራር ኦሳማ ሀምዳን በአሜሪካ የአደራዳሪነት ሚና ላይ ሀማስ እምነት እንዳጣ ተናግረዋል፡፡
ሀምዳን እስካዛሬ በነበሩ የድርድር መድረኮች ላይ የተስማማንባቸውን ሀሳቦች ከመፈጸም ይልቅ አዳዲስ ሀሳቦች እየቀረቡ የድርድሩን ሂደት አረዝመውታል ነው ያሉት፡፡
“የማቀራረብያ ሀሳብ” በሚል በቀረበው ሰነድ ላይ ሁለቱ አካላት የተኩስ አቁም በሚደረግበት ፣ ታጋቾችን እና እስረኞችን በሚለዋወጡበት ሂደት እንዲሁም እስራኤል ከጋዛ ስለምትወጣበት ሁኔታ ላይ በቅድሚያ እንዲስማሙ ይጠይቃል፡፡
የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለዘጠነኛ ጊዜ ወደ ቀጠናው ያቀኑት አንቶኒ ብሊንከን ከኔታንያሁ ባለፈ ከእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄሮዘጌ እና ከመከላከያ ሚንስትሩ ዮቭ ጋለንት ጋር መክረዋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ ወደ ግብጽ እና ወደ ሌሎች የቀጠናው ሀጋራት ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡