የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች በህወሓት ውስጥ ከተፈጠረው የሃሳብ ልዩነት ገለልተኛ እንዲሆኑ ጥሪ ቀረበ
ምርጫ ተካሂዶ መንግስት እስኪቋቋም ድረስ የትግራይ ህዝብ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ደግፈው እንዲቆሙ ጥሪ ቀርቧል
በእነ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን “ህወሓትን መታደግ” በሚል ያካሄደውን ስብሰባ የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቋል
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዝዳንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀ መንብር አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን “ህወሓትን መታደግ” በሚል በመቀሌ ከተማ ያካሄደውን የአንድ ቀን ስብሰባ ትናንት ምሽት አጠናቋል።
በስብሰባው ላይ ህወሓት በመደበኛ ጉባዔው ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት አንስቻቸዋለሁ ያላቸውው አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች ተሳትፈዋል።
“ስብሰባው እየተካሄዱ ባሉ ሁኔታዎች ላይ ግልፅነት ለመፍጠር ያለመ ነው” ሲሉ የትግራይ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሀለፎም መናገራቸውን የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
በእነ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን ትናንት ከጠዋት ጀምሮ ሲያካሂድ የዋለውን የአንድ ቀን ስብሰባ ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ምሽት ላይ አጠናቋል።
በአቋም መግለጫውም “ምርጫ እስኪደረግ እና መደበኛ መንግስት በህዝብ እስኪቋቋም ከፍተኛው የክልሉ አስተዳደር የሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነት ያለው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስር መሆኑን አስታውቋል።
ስለሆነም የትግራይ ህዝብ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን እንዲቆም ጥሪ የቀረበ ሲሆን፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የመልሶ ማቋቋም ፣የተሃድሶ እና የመልሶ ግንባታ ስራዎችን ለማከናወን የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል።
በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተቀባይነት የላቸውም ያለው የእነ አቶ ጌታቸው ቡድን ለሚመጣው አደጋም ይህ ቡድን ኃላፊነት ይወስዳል ብሏል።
“ሰላም የፓርቲያችን እና የህዝባችን ስትራተጂካዊ ምርጫ ነው፤ ህዝባችንን ወደ ጦርነት ለመመለስ ሴራ የሚፈጥር ማንኛውንም የውስጥም ሆነ የውጭ ሃይል አጥብቀን እንቃወማለን” ብሏል የአቋም መግለጫው።
የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ለማስጠበቅና ህዝባችንን ወደ ሙሉ ማገገምና ልማት ለማምጣት ጠንክረን እንሰራለን ያለው የአቋም መግለጫው፤ የክልሉ ህዝብ ምርጫ ተካሂዶ መንግስት እስኪቋቋም ድረስ ጊዚያዊ አስተዳደሩን ደግፈው እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል።
የትግራይ የጸጥታ ሃይሎች በህወሓት ውስጥ ያለውን የሃሳብ ልዩነት ወደ ጎን በመተው የክልሉን ህዝብ ደህንነት እና ሰላም በገለልተኝነት እንዲያስከብሩም ጥሪ ተላልፏል።
በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን እያካሄደ ባለው ጉባኤ የፓርቲው ም/ሊቀመንብር አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የሚሆኑ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በማገድ በተራ አባልነት ከመቀጠል ውጪ በህወሓት ስም ፓለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አይችሉም ማለቱ ይታወሳል።
ፓርቲው ባወጣው መግለጫ" የተለየ ሃሳብ አለኝ "የሚል በጉባኤ ያልተገኘ አካል ወደ ጉባኤው ቀርቦ ሃሳቡን በነፃነት እንዲገልፅ ፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለሚተላለፉት ውሳኔዎች ተገዢ" እንዲሆን ነሃሴ 8/2016 ዓ.ም ጥሪ ማቅረቡን አስታውሷል።
በዚህም የድርጅቱ ጉባኤ ከተሰየመበትና ከተጀመረበት ነሀሴ 7/2016 ዓ.ም ቀን በኋላ ያልተሳተፉ አመራሮች የተራ አባል እንጂ የማእከላዊ ኮሚቴ የሚባል ሃላፊነት የላቸውም ብሏል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ በእነ ዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው ቡድን ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፤ “የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን ለመንጠቅ ሙከራ ሊያደርግ ይችላል” ብለዋል።
አቶ ጌታቸው ከዚህ ቀደም ጉባዔውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ “ፓርቲው ማካሄድ የጀመረው ጠቅላላ ጉባኤ ትግራይን እና ህዝቡን ወደ አደጋ ከመክተት የዘለለ እርባና የለውም” ማለታቸው ይታወሳል።
ህወሓት ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ሲደርሱት የነበሩትን ማስጠንቀቂያዎችን ወደ ጎን በመተተው "የመዳን ጉባኤ" ሲል የሰየመውን 14ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ዛሬ ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል።