ብሊንከን የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸውን በግብጽ ጀመሩ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሶስት ቀናት ቆይታቸው ወደ እስራኤል በማቅናት ከሰሞኑ ዳግም ያገረሸውን ግጭት ለማብረድ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል
እስራኤል ለዩክሬን የድሮን መቃወሚያ መሳሪያዎችን እንድትሰጥ እንደሚያግባቡም ይጠበቃል
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸውን ዛሬ በግብጽ ጀምረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በካይሮ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሜህ ሹክሪ ጋር ይወያያሉ ተብሏል።
ምክክራቸውም የእስራኤል እና ፍልስጤም አመራሮችን በተደጋጋሚ ለማደራደር የሞከረችው ካይሮ በቀጣይም በሚኖራት ሚና ዙሪያ እንደሚያተኩር ነው የተነገረው።
ብሊንከን ከዚህ ምክክር በኋላም በቀጥታ ወደ እስራኤል ያቀናሉ ነው የሚለው ሮይተርስ ዘግቧል።
በዚህም ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር የሚገናኙ ሲሆን፥ ከሰሞኑ ዳግም ያገረሸው ግጭት እንዲቆም የሚያስችሉ ምክክሮችን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ለሪፐብሊካኖች ድጋፋቸውን በማሳየታቸው ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋር የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተው የነበሩት ኔታንያሁ፥ ከባይደን አስተዳደር ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት በጥርጣሬ የሚታይ ነው።
በዌስትባንክ ተጨማሪ የሰፈራ ፕሮግራሞችን ለመጀመር ማሰባቸውም ውጥረቱን ያባብሰዋል ያለችው ዋሽንግተን በያዘችው አቋም ዙሪያ ብሊንከን ከኔታንያሁ ጋር ይነጋገራሉ ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ ራማላህ በማቅናትም ከፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አባስ እና ሌሎች ባለስልጣናት ጋር ምክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
የብሊንከን የሶስት ቀናት የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት ዋነኛ አጀንዳው የእስራኤልና ፍልስጤም ፍጥጫ ነው ቢባልም ሌሎች አጀንዳዎችም ጠረጼዛ ላይ አይጠፉም ይላል የሬውተርስ ዘገባ።
ቀዳሚው እስራኤል ከአረብ ሀገራት ጋር የጀመረችውን ግንኙነት የማስተካከል እንቅስቃሴ ማጠናከር ላይ ያተኩራል።
11ኛ ወሩን በያዘው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ቴል አቪቭ ለኬቭ የድሮን መቃወሚያ መሳሪያዎችን እንድትልክ ማግባባትም ሌላኛው የንግግሩ አካል እንደሚሆን ተገምቷል።