በወር አንዴ መካከለኛው ምስራቅን የሚጎበኙት ብሊንከን ለጋዛው ጦርነት ለምን መፍትሄ አጡ?
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዶሃ ዳግም በተጀመረው የተኩስ አቁም ድርድር ዙሪያ ከሳኡዲና ግብጽ መሪዎች ጋር ይመክራሉ ተብሏል
ዋሽንግተን እስራኤል በራፋህ የእግረኛ ጦር እንዳታስገባ ብትጠይቅም ኔታንያሁ ጦርነቱ አይቀሬ ነው ብለዋል
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ስድስተኛውን የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸውን ዛሬ ይጀምራሉ።
በአማካይ በወር አንድ ጊዜ ወደ ቀጠናው የዘለቁት ብሊንከን አስከፊውን ጦርነት ማስቆም የሚያስችል መፍትሄ አላገኙለትም።
ሀገራቸውም ለዋነኛ አጋሯ እስራኤል በአንድ እጇ የጦር መሳሪያ በገፍ እያቀረበች በሌላኛው ተኩስ እንዲቆም በጸጥታው ምክርቤት የሚቀርቡ የውሳኔ ሃሳቦችን ድምጽም በድምጽ የመሻር ስልጣኗ ውድቅ ታደርጋለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ፕሬዝዳንት ባይደንን ጨምሮ የተለያዩ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁን መቃወም ጀምረዋል።
በተለይ እስራኤል በራፋህ የእግረኛ ጦር አስገብቼ ሃማስን ካልደመሰስኩ ጦርነቱ አይቆምም ማለቷ ሊያደርስ የሚችለው ሰብአዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑንም በመጥቀስም “ኔታንያሁን ከስልጣን አንሱት” የሚሉ ጥሪዎችን እያቀረቡ ነው።
የዛሬው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የመካከለኛው ምስራቅ ጉዞም ረሃብን እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመች ነው በሚል ወቀሳ የቀርበባት እስራኤል ተኩስ እንድታቆምና ሰብአዊ ድጋፍ እንዲገባ እንድትፈቅድ ለማግባባት ያለመ ነው ተብሏል።
በርግጥ ብሊንከን በአሁኑ ጉዟቸው ወደ ቴል አቪቭ ባያቀኑም በጂዳ እና ካይሮ ቆይታቸው በኳታር በቀጠለው የተኩስ አቁም ድርድር ዙሪያ እንደሚወያዩ ሬውተርስ ዘግቧል።
ዋይትሃውስ በረመዳን ጾም መግቢያ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚደረስ ይፋ ቢያደርግም እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ጥቃቷን አጠናክራ መቀጠል በመፈለጓ ሳይሳካ ቀርቷል።
የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) ሃላፊ ዴቪድ ባርኔ በዶሃ ከግብጽ እና ኳታር አደራዳሪዎች ጋር ከሰኞ ጀምሮ መምከር ቢጀምሩም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረሳል ተብሎ አይጠበቅም።
እስራኤል በአል ሺፋ ሆስፒታል እና በራፋህ ጥቃት መፈጸሟን መቀጠሏም የዶሃውን ንግግር ጥቁር ጥላ እንዳጠላበት የሃማስ የፖለቲካ መሪው ኢስማኤል ሃኒየህ መናገራቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በሰሜናዊ ጋዛ ከ300 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን በቀጣዩ ግንቦት ወር ለረሃብ መጋለጣቸው አይቀሬ ሆኗል።
በድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ቢሮ ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ፥ እስራኤል እርዳታ እንዳይገባ በማድረግ ጥቃት ማድረሷን መቀጠሏ “ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመች መሆኑን ሊያመላክት የሚችል ነው” ብለዋል።
ረሃብ ከጦርነቱ በበለጠ የፍልስጤማውያንን ህይወት እንዳይቀጥፍ አለማቀፍ ጥሪው ቢቀጥልም እስራኤል ሃማስን ካላጠፋሁ የሚል ተደጋጋሚ አመክንዮ እያቀረበች ድብደባዋን ቀጥላለች።