የእስራኤሉ ሞሳድ ኃላፊ በተኩስ አቁም ጉዳይ በኳታር ከአደራዳሪዎች ጋር ሊነጋገሩ ነው
ሀማስን ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ የምትለው እስራኤል በግብጽ ድንበር ያለችውን ራፋን ለማጥቃት የያዘቸውን እቅድ አጽድቃለች
የሞሳድ ኃላፊው ዴቪድ ባርኒያ ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከግብጹ ባለስልጣናት ጋር ይነጋገራሉ
የእስራኤሉ ሞሳድ ኃላፊ በተኩስ አቁም ጉዳይ በኳታር ከአደራዳሪዎች ጋር ሊነጋገሩ ነው።
የእስራኤል የስለላ ድርጅት(ሞሳድ) ኃላፊ በነገው እለት በኳታር ዶሃ ከአደራዳሪዎች ጋር በተኩስ አቁም ጉዳይ እንደሚነጋገሩ ሮይተርስ ዘግቧል።
ኃላፊው በቅርቡ ሀማስ ባቀረበው የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ ላይም ምላሽ ይሰጣሉ ተብሏል።
ሮይተርስ ያናገራቸው ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ የሞሳድ ኃላፊው ዴቪድ ባርኒያ ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከግብጹ ባለስልጣናት ጋር በሚያደርጉት ንግግር በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ትኩረት ይደረጋል።
እስራኤል በትናንትናው እለት ተደራዳሪ ልኡክ ወደ ኳታር እንደምትልክ ብትገልጽም መቼ እንደምትልክ እና እነማን እንደሚሳተፉ ግልጽ አላደረገችም ነበር።
በኳታር ይደረጋል ከተባለው ንግግር በፊት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያማን ኔታንያሁ የጸጥታ ካቢኔያቸውን ሰብስበው እንደሚወያዩ ተገልጿል።
በርኒያ ከዚህ በፊት በነበሩ ወሳኝ የሚባሉ የድርድር ምዕራፎች ተካፍለዋል።
ባለፈው ህዳር በኳታር አደራዳሪነት በተደረሰው የአጭር ቀናት ተኩስ አቁም ስምምነት እኝህ ኃላፊ ተሳትፈው ነበር። ኃላፊ ባለፈው ጥር ወር ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው የጊዜያዊ ተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ሀማስ ሳይቀበለው ቀርቷል።
ሀማስ በዚህ ሳምንት የእስራኤል ታጋቾች በፍልስጤማውያን እስረኞች የሚለወጡበትን ዝርዝር ሁኔታ ለአደራዳሪዎቹ እና የእስራአል አጋር ለሆነችው አሜሪካ አቅርቧል።
ነገርግን እስራኤል ሀማስ ያቀረበውን የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ "እወነታ ላይ ያልተመሰረተ ነው" በማለት እንደማትቀበለው ገልጻለች።
በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ታጋቾች እንዲለቀቁ በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም እስካሁን አልተሳኩም።
ሀማስን ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ የምትለው እስራኤል በግብጽ ድንበር ያለችውን ራፋን ለማጥቃት የያዘቸውን እቅድ አጽድቃለች።