በሰሜናዊ ጋዛ ህጻናት በረሃብ እየሞቱ ነው - ዶክተር ቴድሮስ
የአለም ጤና ድርጅት ከጥቅምት ወር ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋዛ ሆስፒታሎች ያደረገው ጉብኝትም አሳዛኝ ነገሮችን የተመለከተበት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል
በእስራኤል ከተገደሉ ከ30 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ከ12 ሺህ 600 በላዩ ህጻናት ናቸው
በሰሜናዊ ጋዛ ህጻናት በረሃብ እየሞቱ መሆኑን የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገለጹ።
ድርጅቱ እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የአል አውዳ እና ካማል አድዋን ሆስፒታሎችን ጎብኝቷል።
በጉብኝቱ “አሳዛኝ ግኝቶች” ነበሩ ያሉት ዶክተር ቴድሮስ፥ ህጻናት በረሃብና በአልሚ ምግብ እጦት ህይወታቸው እያለፈ መሆኑን በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
Grim findings during @WHO visits to Al-Awda and Kamal Adwan hospitals in northern #Gaza: severe levels of malnutrition, children dying of starvation, serious shortages of fuel, food and medical supplies, hospital buildings destroyed.
— Tedros Adhanom Ghebreyesus (@DrTedros) March 4, 2024
The visits over the weekend were the first… pic.twitter.com/CxaCuau7iR
በሃማስ የሚተዳደረው የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር በከማል አድዋን ሆስፒታል በውሃ ጥም እና የአልሚ ምግብ እጥረት 15 ህጻናት ህይወታቸው ማለፉን አስታውቋል።
በደቡባዊ ጋዛ ከተማዋ ራፋህም 16ኛው ህጻን በሆስፒታል ውስጥ በረሃብ መሞቱን የፍልስጤም የዜና ወኪል ዋፋ ዘግቧል።
የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ቴድሮስ 300 ሺህ የሚሆን ህዝብ የሚበላና የሚጠጣ ባጣበት ሰሜናዊ ጋዛ ህጻናት በረሃብ እየሞቱ መሆኑንና የወደሙ ሆስፒታሎችም ከፍተኛ የህክምና ቁሳቁስ እጥረት እንደገጠማቸው አብራርተዋል።
“የምግብ እጥረት የ10 ህጻናትን ህይወት ቀምቷል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ እስራኤል የሰብአዊ ድጋፍ ወደ ጋዛ ሳይቆራረጥ እንዲገባ ልትፈቅድ ይገባል ብለዋል።
የአለም ጤና ድርጅት በሰሜናዊ ጋዛ ቅኝት ለማድረግ ያቀረበው ጥያቄ ሳይፈቀድለት መቆየቱን የቢቢሲ ዘገባ አስታውሷል።
በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ህይወታቸው ካለፈ ከ30 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ውስጥ ከ12 ሺህ 600 በላዩ ህጻናት ናቸው ተብሏል።
ከእስራኤል ድብደባ የተረፉ ህጻናት አሁን በረሃብ እየሞቱ ነው።
የመንግስታቱ ድርጅትም በጋዛ አስከፊ ረሃብ መከሰቱ “አይቀሬ” ነው ሲል ያስጠነቀቀ ሲሆን፥ ከ570 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን (የጋዛ አንድ አራተኛ ህዝብ) በከፍተኛ የምግብ እጦት ውስጥ ነው ተብሏል።
የተመድ የእርዳታ ድርጅቶች አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ የሰብአዊ ድጋፍ በብዛት እንዲገባ ቢጠይቁም ተፋላሚዎቹ እስካሁን ስምምነት ላይ አልደረሱም።
በረመዳን ጾም መጀመሪያ ይደረሳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የተኩስ አቁም ድርድርም በካይሮ ያለ እስራኤል ተሳትፎ እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።