ብሊንከን ከፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ጋር በራማላህ ተወያዩ
ፕሬዝዳንቱ ዋሽንግተን በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ በቴል አቪቭ ላይ ጫና እንድታደርግ ጠይቀዋል
አሜሪካ ግን የተኩስ አቁሙ ሃማስ ዳግም እንዲደራጅ ያደርገዋል በሚል ጥያቄውን ውድቅ አድርጋለች
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በዛሬው እለት በዌስትባንክ ያልተጠበቀ ጉብኝት አድርገዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በራማላህ ከፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ጋርም መወያየታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ብሊንከን ከፕሬዝዳንት አባስ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ፍልስጤማውያን ከጋዛ በሃይል መፈናቀል” እንደሌለባቸው መናገራቸውን ቃል አቀባያቸው ተናግረዋል።
በዌስትባንክ በየቀኑ እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት ማርገብ እንደሚገባም ነው ያነሱት።
ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ በበኩላቸው እስራኤል በጋዛ “የዘር ፍጅት” እየፈጸመች መሆኑንና አለማቀፋዊ ህጎችን መጣሷን መቀጠሏን ማብራራታቸውን የፍልስጤም የዜና ወኪል ዋፋ ዘግቧል።
የፍልስጤም አስተዳደር በጋዛ ወደ ስልጣን የሚመለሰው የእስራኤልና ፍልስጤም ግጭት “ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ መፍትሄ” ሲፈለግለት ብቻ ነውም ብለዋል።
እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን የአየር ድብደባ እና ምድር ውጊያ እንድታቆም ዋሽንግተን ግፊት እንድታደርግም ጠይቀዋል ይላል የፍራንስ 24 ዘገባ።
ይሁን እንጂ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዎንታዊ ምላሽ አላገኙም።
በትናንትናው እለት በዮርዳኖስ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሳኡዲ፣ ግብጽ፣ ኳታር እና ዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የመከሩት ብሊንከን እስራኤል በጋዛ ተኩስ እንድታቆም የቀረበውን ጥሪ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።
አሜሪካ ከዚህ ቀደምም በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት በጋዛ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረስ የቀረቡ የውሳኔ ሃሳቦችን መቃወሟ አይዘነጋም።
ዋሽንግተን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሃማስን ጊዜ በመስጠት ራሱን እንዲያደራጅ መፍቀድ ነው በማለት ቴል አቪቭ የጀመረችውን የአየር እና ምድር ዘመቻ እንድትገፋበት ደግፋለች።
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 9 ሺህ 770 መድረሱን አመላክቷል።