“የፍልስጤሙ ማንዴላ” ማርዋን ባርጉቲ ማን ነው?
ከ20 አመት በላይ በእስራኤል እስር ቤት ውስጥ ያለው ባርጉቲ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖችን በማቀራረብ ይታወቃል
ሃማስ እስራኤል ያሰረቻቸውን ከ11 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን እንድትለቅ ጠይቋል
የፍልስጤሙ ሃማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት አድርሶ 1 ሺህ 400 ሰዎችን ከገደለና ከ200 በላይ እስራኤላውያንን ካገተ በኋላ ለቴል አቪቭ ከባድ ጥያቄ አቅርቧል።
ሃማስ የእስራኤልን እስር ቤቶች የሞሉ ፍልስጤማውያን ካልተለቀቁ ያገታቸውን ሰዎች እንደማይለቅ ነው ያስታወቀው።
በእስራኤል እስር ቤት ውስጥ ከሚገኙት ፍልስጤማውያን መካከል ማርዋን ባርጉቲ ይገኝበታል።
“የፍልስጤም ኔልሰን ማንዴላ” የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ማርዋን ባርጉቲ ማን ነው?
ባርጉቲ በፈረንጆቹ 2002 በእስራኤል የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ውሎ አሁንም ድረስ በእስር ላይ የሚገኝ ፍልስጤማዊ ነው።
የፋታህ የወታደራዊ ክንፍ መሪ የነበረው ማርዋን ባርጉቲ በበርካታ የግድያ ወንጀሎች እና የሽብርተኛ ቡድን አባል ሆነሃል በሚሉ ክሶች ዘብጥያ ከወረደ 21 አመታት ተቆጥረዋል።
የፍልስጤም እና እስራኤል ግጭት በተነሳ ቁጥር ስሙ ተደጋግሞ የሚጠቀሰው ባርጉቲ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖችን ለማቀራረብ በብዙው የደከመ መሪ ነው።
ከፋታህ፣ ሃማስ፣ ኢስላሚክ ጂሃድ እና ሌሎች ቡድኖች አባል ከነበሩ እስረኞች ጋር በፈረንጆቹ 2006 ይፋ ያደረገው የፍልስጤም እጣ ፈንታን የሚያቃና ሰነድም ከስራዎቹ መካከል ተጠቃሽ ነው።
ሰነዱ ነጻዋ ፍልስጤም በፈረንጆቹ 1967 በተካለለው ድንበር መሰረት እንድትመሰረት የሚጠይቅ ሲሆን፥ የነጻነት ትግሎችም ከ1967 በፊት የተያዙ ስፍራዎችን ሊያካትት አይገባም ይላል።
ሃማስ በ2006 በምርጫ ካሸነፈ በኋላ በፋታህ እና ሃማስ መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማቆምም የጥምር መንግስት እንዲቋቋም ይጠይቃል።
ማርዋን ባርጉቲ እስር ቤት ከመግባቱ በፊትም የፍልስጤም የፖለቲካ ሃይሎችን ለማቀራረብ ሁነኛውና ተቀባይነት የነበረው ሰው መሆኑን ፍራንስ 24 በዘገባው አመላክቷል።
የፋታህ መሪ እያለ ከሃማስ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ያደረገው ጥረትም በፋታህ የሚደገፍ እንዳልነበር ነው የሚነገረው።
ያሲር አራፋትን የተኩት የ88 አመቱ የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አባስ ምርጫ እንዲደረግ አለመፍቀዳቸው እንጂ ባርጉቲ በፍልስጤማውያን ዘንድ ቀዳሚው ተመራጭ እንደሚሆኑም የበርካቶች እምነት ነው።
ከሁለት አስርት አመት በላይ በእስር ቤት ማሳለፋቸውና የፍልስጤም ተቀናቃኝ ሃይሎችን ለማቀረርብ ያደረጉት ጥረት “የፍልስጤሙ ማንዴላ” የሚል ቅጽል ስም ያሰጣቸው ባርጉቲ፥ ከሙሃመድ አባስም ሆነ ከሃማሱ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ በላይ ተቀባይነት እንዳላቸው የቅርብ ጊዜ ጥናቶች ጠቁመዋል።
ማርዋን ባርጉቲ ከእስር ይለቀቁ ዘንድ ባለቤታቸው ፋድዋ ባርጉቲ በነሃሴ ወር 2023 አዲስ ዘመቻ ቢከፍቱም ከእስራኤል በኩል ምላሽ አልተሰጠም።
ባርጉቲ ተቀናቃኝ ሃይሎችን የማስማማት ተሰጥኦ አላቸው የሚባልላቸው ሲሆን፥ የአደራዳሪነት ብቃታቸውንና የሰላም ቀናኢነታቸውን በመጥቀስ የኖቬል ሽልማት እጩ እንዲሆኑም በተደጋጋሚ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ “የፍልስጤሙ ማንዴላ” እስካሁን ከእስር አልተለቀቁም፤ የኖቬል የሰላም ሽልማትም አልተበረከተላቸውም።
ሃማስ ከ29 ቀናት በፊት በተቀሰቀሰው ጦርነት ያገታቸውን እስራኤላውያን ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ተከትሎም ይፈታሉ ተብሎ አይጠበቅም።