በመቶዎች የሚቆጠሩት ሰልፈኞች "አሁኑኑ እሰሩት" የሚል ድምጽ በማሰማት በኔታንያሁ ቤት ዙሪያ ያሉትን ፖሊሶች ሲገፉ ታይተዋል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠሟቸዋል።
ጦርነት እየመሩ ያሉት ኔታንያሁ ላይ እየቀረበ ያለው ተቃውሞ እየበረታ መሄዱንም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
ባለፈው ወር ሀማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ በጋዛ ሰርጥ አካባቢ ባሉ ማህበረሰቦች ላይ ጥቃት እንዲደረስ ምክንያት በሆነው ውድቀት የተቆጡ እስራኤላውያን በኔታንያሁ መኖሪ ቤት ፊትለፊት በመሰለፍ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የእስራኤልን ሰንደቅ አላማ የሚያውለበልቡት በመቶዎች የሚቆጠሩት ሰልፈኞች "አሁኑኑ እሰሩት" የሚል ድምጽ በማሰማት በቤቱ ዙሪያ ያሉትን ፖሊሶች ሲገፉ ታይተዋል።
ይህ ሰልፍ 1/3 የሚሆነው ህዝብ ኔታንያሁ ስልጣን እንዲለቁ እንደሚፈልግ ከሚያሳየው ሰርቬይ ጋር መገጣጠሙ፣ ህዝቡ በጸጥታ እና በፖለቲካ መሪዎች ላይ ምን ያህል እንደተበሳጨ የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር ያልተጠበቀ ጥቃት በመሰንዘር 1400 ዜጎችን እንዲገድል እና 240 ሰዎችን አግቶ እንዲወስድ ምክንያት ለሆነው ክፍተት መፈጠር በግላቸው ኃላፊት እንደሚወስዱ ተናግረዋል።
ድርጊቱ ሲፈጠር የነበረው የህዝብ ቁጣ እየቀነሰ ሄዶ የነበረ ቢሆንም ቤተሰቦቻቸው የታገቱባቸው ሰዎች መንግስትን አምረረው ሲተቹ ቁጣው እንደገና ሊጨምር ችሏል።
በእስራኤል ዋና ከተማ ቴልአቪቭ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሰንደቅአለማ እና የበርካታ ታጋቾችን ፎቶ በማውለብለብ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
እስራአል ማጥቃቷን የምትቀጥል ከሆነ የታጋቾች ህይወት አደጋ ውስጥ ስለሚወድቅ ጉዳዩ በንግግር መፍትሄ ይበጅለት የሚሉ ወገኖች ነበሩ።
ታጋቾቹን ማስለቀቅ የሚቻለው ሀማስን በማጥቃት መሆኑን የምትገልጸው እስራኤል ግን በጋዛ ገብታ ከሀማስ ታጣቂዎችን ውጊያ እያካሄደች ነው።
ሀማስ በእገታ ከያዛቸው 239 ሰዎች ውስጥ በእስራኤል የአየር ጥቃት 60 ያህሉ እንደጠፉበት ትናንት አስታውቋል።
እስራኤል በጋዛ ተኩስ እንድታቆም የቀረበላትን አለምአቀፍ ጥሪ ውድቅ አድርጋዋለች።