ምርጫ ቦርድ በዚህ አመት ለማካሄድ አቅዷቸው የነበሩ ምርጫዎችን ማራዘሙ ተገለጸ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራትን እቅድ አፈጻጸሙን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል
ቦርዱ ምርጫዎቹን ወደ 2016 ዓ.ም ለማራዘም መገደዱን ምክትል ሰብሳቢው ተናግረዋል
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በዚህ አመት ለማካሄድ አቅዷቸው የነበሩ ምርጫዎችን ማራዘሙን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራትን እቅድ አፈጻጸሙን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።
ቦርዱ በዚህ ጊዜ እንዳለውም በተያዘው ዓመት በጸጥታ እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች የክልል ምክር ቤት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ለማካሄድ አቅዶ ነበር ብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የአካባቢያዊ ምርጫ ለማካሄድም ቦርዱ እቅድ የነበረው ቢሆንም በዚህ ዓመት ማካሄድ አለመቻሉንም በሪፖርቱ ላይ ገልጿል፡፡
ቦርዱ በዚህ ዓመት አካሂዳለሁ ያላቸው የምክር ቤቶች እና አካባቢያዊ ምርጫዎች እንዳይካሄዱ ኢቲቪ የቦርዱን ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ጠቅሶ ዘግቧል።
ቦርዱ ምርጫዎቹን ወደ 2016 ዓ.ም ለማራዘም መገደዱን ሰብሳቢው መግለጻቸውን ኢትቪ ዘግቧል፡፡
የጸጥታ ችግሮች፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ እንዳያካሂዱ መከልከላቸው እና በሌሎችም ምክንያቶች በዚህ ዓመት ይካሄዳሉ የተባሉ ምርጫዎችን ወደሚቀጥለው ዓመት እንዲራዙ ያደረጉ ዋነኛ ምክንያች እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
ምርጫ ቦርድ የፌደሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ክልል ያሉ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች አዲስ ክልል እናዋቅር የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት የህዝበ ውሳኔ ያካሄደ ሲሆን በወላይታ ዞን የሕግ ጥሰት ተፈጽሟል በሚል ህዝበ ውሳኔው እንዲደገም መወሰኑ ይታወሳል፡፡